2 Kings 9

ኢዩ ተቀብቶ በእስራኤል ላይ ነገሠ

1ነቢዩ ኤልሳዕ ከነቢያት ማኅበር አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ወገብህን ታጥቀህ፣ ይህን የዘይት ማሰሮ በመያዝ በሬማት ወደምትገኘው ገለዓድ ሂድ። 2በዚያም ስትደርስ የናሜሲን የልጅ ልጅ፣ የኢዮሣፍጥን ልጅ ኢዩን ፈልገው። ወደ እርሱም ቀርበህ ከጓደኞቹ ለብቻ ከነጠልኸው በኋላ፣ ወደ እልፍኝ አስገባው። 3ከዚያም ማሰሮውን ይዘህ ዘይቱን በራሱ ላይ አፍስስና፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ እኔ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀባሁህ” ’ ብለህ ዐውጅ። ከዚያም በሩን ከፍተህ ሩጥ፤ ፈጽሞ አትዘግይ።”

4ስለዚህ ጕልማሳው ነቢይ በሬማት ወደምትገኘው ገለዓድ ሄደ። 5በዚያ እንደ ደረሰም፣ የሰራዊቱ ጦር መኰንኖች በአንድነት ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም “መኰንን ሆይ፤ ወደ አንተ ተልኬአለሁ” አለ።

ኢዩም፣ “ለማንኛችን ነው?” ሲል ጠየቀ።

እርሱም፣ “መኰንን ሆይ፤ ለአንተ ነው” ብሎ መለሰ።

6ኢዩም ተነሥቶ ወደ ቤት ገባ፤ ከዚያም ነቢዩ ዘይቱን በኢዩ ላይ አፈሰሰና እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀብቼሃለሁ። 7የአገልጋዮቼን የነቢያትን ደም እንዲሁም የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ደም ሁሉ ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ አንተ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ። 8የአክዓብ ቤት በሙሉ ይጠፋል፤ ባሪያም ይሁን ተወላጅ፣ በእስራኤል የሚገኘውን
ወይም ማንኛውም ገዥ ወይም መሪ
የመጨረሻ ወንድ ልጅ ሁሉ ከአክዓብ እቈርጣለሁ።
9ከእንግዲህ የአክዓብን ቤት፣ እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፣ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ። 10ኤልዛቤልን ግን በኢይዝራኤል ዕርሻ ውሾች ይበሏታል፤ የሚቀብራትም አይኖርም።’ ” ይህን ተናግሮም መዝጊያውን ከፍቶ ሮጠ።

11ኢዩ ወጥቶ የጦር አለቆች ወደ ሆኑት ጓደኞቹ እንደ ደረሰ፣ ከመካከላቸው አንዱ “ሁሉም ነገር ሰላም ነው? ይህ እብድ ወደ አንተ የመጣው ለምንድን ነው?” ሲል ጠየቀው።

ኢዩም “ሰውየውንም ሆነ የሚናገረውን እናንተም ታውቃላችሁ” ሲል መለሰ።

12እነርሱም፣ “ይህማ ትክክል አይደለም፤ ይልቅስ እውነቱን ንገረን” አሉት።

ኢዩም እንዲህ አለ፤ “እርሱ የነገረኝማ ይህ ነው፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የእስራኤል ንጉሥ እንድትሆን ቀብቼሃለሁ።’ ”

13ከዚያ ሁሉም ቶሎ ብለው ልብሳቸውን እያወለቁ በሚራመድበት ደረጃ ላይ አነጠፉ፤ ከዚያም መለከት ነፍተው፣ “ኢዩ ነግሧል” አሉ።

ኢዩ ኢዮራምንና አካዝያስን ገደለ

9፥21-29 ተጓ ምብ – 2ዜና 22፥7-9 14ስለዚህ የናሜሲ የልጅ ልጅ፣ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ በኢዮራም ላይ አሤረ። በዚህ ጊዜ ኢዮራምና እስራኤል ሁሉ በሬማት የምትገኘውን ገለዓድን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጥቃት ለማዳን ይጠብቁ ነበር። 15ንጉሥ ኢዮራም
ዕብራይስጡ ይሆራም ተለዋጩ ትርጕም ያሮም ይለዋል።
ግን የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን ጦርነት በገጠመው ጊዜ፣ ሶርያውያን ካደረሱበት ቍስል ለማገገም ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም፣ “እንግዲህ ሐሳባችሁ እንዲህ ከሆነ፣ ይህን ነገር ወደ ኢይዝራኤል ሄዶ እንዳይናገር፣ ማንም ሰው ከዚህች ከተማ ሾልኮ እንዳይወጣ ጠብቁ” አለ።
16ከዚያም በሠረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ ይህን ያደረገውም ኢዮራም በዚያ ስለ ተኛና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም እርሱን ለመጠየቅ ወደዚያው ስለ ወረደ ነው።

17በኢይዝራኤል ግንብ ማማ ላይ የቆመው ጠባቂ የኢዩ ወታደሮች መቅረባቸውን አይቶ፣ “ኧረ ወታደሮች መጡ” በማለት ጮኾ ተናገረ።

ኢዮራምም፣ “አንድ ፈረሰኛ ተጠርቶ፤ እንዲገናኛቸው ላኩትና፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሎ ይጠይቅ” ሲል አዘዘ።

18ፈረሰኛውም ኢዩን ለመገናኘት ጋልቦ ሄደና፣ “ንጉሡ፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሏል” አለው።

ኢዩም፣ “ስለ ሰላም መጨነቅ የአንተ ጕዳይ አይደለም! ይልቅስ ወደ ኋላ ዕለፍና ተከተለኝ” አለው።

ጠባቂውም፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሷል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ብሎ አሳወቀ።

19ስለዚህ ንጉሡ ሌላ ፈረሰኛ ላከ፤ ወደ እነርሱ ዘንድ እንደ ደረሰም፣ “ንጉሡ፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ይላል” አለው።

ኢዩም “ስለ ሰላም መጨነቅ የአንተ ጕዳይ አይደለም! ይልቅስ ወደ ኋላ ዕለፍና ተከተለኝ” አለው።

20ጠባቂው፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሷል፤ ነገር ግን ይህም ተመልሶ አልመጣም፤ የወታደሮቹ መሪ ሠረገላ አነዳዱ ልክ እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ አነዳድ ነው፤ ሲነዳም እንደ እብድ ነው” ሲል አሳወቀ።

21ኢዮራምም፣ “በሉ ሠረገላዬን አዘጋጁ” ብሎ አዘዘ። ሠረገላው እንደ ተዘጋጀም፣ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራምና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ በየሠረገሎቻቸው ሆነው ኢዩን ለመገናኘት ሄዱ፤ የኢይዝራኤላዊው የናቡቴ ርስት በነበረው ዕርሻ ላይም ተገናኙት። 22ኢዮራምም ኢዩን ገና ሲያየው፣ “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀው።

ኢዩም፣ “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” ሲል መለሰ።

23ኢዮራምም ሠረገላውን አዙሮ በመሸሽ፣ “አካዝያስ ሆይ፤ ይህ ክዳት ነው!” አለ።

24ከዚያም ኢዩ ቀስቱን በማስፈንጠር ኢዮራምን በትከሻና ትከሻው መካከል ወጋው፤ ፍላጻውም ዘልቆ ልቡን ስለ ወጋው፣ ሠረገላው ውስጥ ዘፍ ብሎ ወደቀ።

25ኢዩም የሠረገላ ኀላፊውን ቢድቃርን እንዲህ አለው፤ “አንሣውና በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ ዕርሻ ላይ ጣለው፤ አንተና እኔ አባቱን አክዓብን በየሠረገሎቻችን ሆነን ተከትለነው ስንሄድ፣ እግዚአብሔር ይህን ትንቢት እንዲህ ሲል እንደ ተናገረበት አስታውስ፤ 26‘ትናንት የናቡቴንና የልጆቹን ደም አይቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር’ ይህንም በዚሁ ዕርሻ ላይ በርግጥ አንተው እንድትከፍል አደርግሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር አሁንም በእግዚአብሔር ቃል በተነገረው መሠረት አንሣውና በዚሁ ዕርሻ ውስጥ ጣለው።”

27የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ይህን ሲያይ፣ ወደ ቤት ሀጋን በሚያወጣው መንገድ ሸሸ፤
ወይም በአትክልቱ ስፍራ በሚገኘው በኩል ሸሸ
ኢዩም እያሳደደ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እርሱንም ግደሉት!” አለ። እነርሱም በይብለዓም ከተማ አጠገብ በጉር ዐቀበት መንገድ ላይ በሠረገላው ውስጥ እንዳለ አቈሰሉት፤ እርሱ ግን ወደ መጊዶ ሸሽቶ፤ እዚያው ሞተ።
28አገልጋዮቹም በሠረገላ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር በመቃብሩ ቀበሩት። 29አካዝያስ በይሁዳ የነገሠው፣ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር።

ኤልዛቤል ተገደለች

30ከዚያም ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤ ኤልዛቤልም ይህን በሰማች ጊዜ ዐይኗን ተኳኵላ፣ ጠጕሯንም አሰማምራ በመስኮት ትመለከት ነበር። 31ኢዩ የቅጥሩን በር ዐልፎ ሲገባ፣ “ጌታህን የገደልህ አንተ ዘምሪ የመጣኸው በሰላም ነውን?”
ወይም፣ ጌታውን የገደለው ዘምሪ ሰላም አለውን?
ስትል ጠየቀችው።

32ቀና ብሎ ወደ መስኮቱ ተመለከተና፣ “ማነህ አንተ? ማነው የሚተባበረኝ” ሲል ጮኾ ተጣራ። ሁለት ሦስት ጃንደረቦችም ቍልቍል ወደ እርሱ ተመለከቱ፤ 33ኢዩም፣ “ወደ ታች ወርውሯት!” አለ፤ እነርሱም ወረወሯት፤ ፈረሶቹ ሲረጋግጧትም ደሟ በግንቡና በፈረሶቹ ላይ ተረጨ።

34ኢዩም ገብቶ በላ፤ ጠጣም። ከዚያም፣ “ምንም ቢሆን የንጉሥ ልጅ ናትና ይህችን የተረገመች ሴት በሚገባ ቅበሯት” አለ። 35ሊቀብሯት ሲወጡ ግን ከራስ ቅሏ፣ ከእግሯና ከእጇ በቀር ሌላ ያገኙት አልነበረም። 36ተመልሰውም ይህን ሲነግሩት፣ ኢዩ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ለባሪያው ለቴስቢያዊው ለኤልያስ፣ ‘በኢይዝራኤል ምድር ዕርሻ ውስጥ ውሾች የኤልዛቤልን ሥጋ ይበሉታል፤ 37ሥጋዋም በኢይዝራኤል ምድር ዕርሻ ውስጥ እንደ ፍግ ስለሚሆን፣ ማንም ሰው፣ “ይህች ኤልዛቤል ናት” ሊል አይችልም’ ብሎ የተናገረው ቃል ይህ ነው።”

Copyright information for AmhNASV