Ezekiel 31

የሊባኖስ ዝግባ

1በዐሥራ አንደኛው ዓመት፣ በሦስተኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖንና ስፍር ቍጥር ለሌለው ሕዝቡ እንዲህ በል፤

“ ‘በክብር ከአንተ ጋር ማን ሊወዳደር ይችላል?
3ለጫካው ጥላ የሆኑ የሚያማምሩ ቅርንጫፎች የነበሩትን፣
እጅግ መለሎ ሆኖ፣
ጫፉ ሰማይ የደረሰውን፣
የሊባኖስን ዝግባ አሦርን ተመልከት።
4ውሆች አበቀሉት፤
ጥልቅ ምንጮች አሳደጉት፤
ጅረቶቻቸው ፈሰሱ፤
የሥሮቹንም ዙሪያ ሁሉ አረሰረሱ፤
በመስኩ ላይ ወዳሉት ዛፎች ሁሉ፣
መስኖዎቻቸውን ለቀቁት።
5ስለዚህ በደን ካሉት ዛፎች ሁሉ፣
እጅግ ከፍ አለ፤
ቅርንጫፎቹ በዙ፤
ቀንበጦቹ ረዘሙ፤
ከውሃውም ብዛት የተነሣ ተስፋፉ።
6የሰማይ ወፎች ሁሉ፣
በቅርንጫፎቹ ላይ ጐጇቸውን ሠሩ፤
የምድር አራዊት ሁሉ፣
ከቅርንጫፎቹ ሥር ግልገሎቻቸውን ወለዱ።
ታላላቅ መንግሥታትም ሁሉ፣
ከጥላው ሥር ኖሩ።
7ከተንሰራፉት ቅርንጫፎቹ ጋር፣
ውበቱ ግሩም ነበር፤
ብዙ ውሃ ወዳለበት፣
ሥሮቹ ጠልቀው ነበርና።
8በእግዚአብሔር ገነት ያሉ ዝግባዎች፣
ሊወዳደሩት አልቻሉም፤
የጥድ ዛፎች፣
የእርሱን ቅርንጫፎች አይተካከሉትም፤
የአስታ ዛፎችም፣
ከእርሱ ቅርንጫፎች ጋር አይወዳደሩም፤
በእግዚአብሔር ገነት ያለ ማናቸውም ዛፍ፣
በውበት አይደርስበትም።
9በብዙ ቅርንጫፎች፣
ውብ አድርጌ ሠራሁት፤
በእግዚአብሔርም የአትክልት ቦታ፣
በገነት ያሉትን ዛፎች የሚያስቀና አደረግሁት።
10“ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጥቅጥቅ ባለው ቅጠል ላይ ጫፉን ከፍ በማድረግ ራሱን በማንጠራራቱ፣ በርዝማኔውም በመኵራራቱ፣ 11እንደ ክፋቱ መጠን የሥራውን ይከፍለው ዘንድ፣ ለአሕዛብ ገዥ አሳልፌ ሰጠሁት። አውጥቼ ጥዬዋለሁ፤ 12ከአሕዛብ ወገን እጅግ ጨካኝ የሆኑትም ባዕዳን ሰዎች ቈራርጠው ጣሉት። ቀንበጦቹ በተራራዎቹና በሸለቆዎቹ ሁሉ ላይ ወድቀዋል፤ ቅርንጫፎቹም በውሃ መውረጃዎቹ ሁሉ ላይ ተሰባብረው ወድቀዋል፤ የምድሪቱ ሰዎች ሁሉ ከጥላው ሥር በመውጣት ትተውት ሄደዋል። 13የሰማይ ወፎች ሁሉ በወደቀው ዛፍ ላይ ሰፈሩ፤ የምድር አራዊት ሁሉ በወደቀው ዛፍ ቅርንጫፎች ላይ ሰፈሩ። 14ስለዚህ በውሃ አጠገብ ያለ ማንኛውም ዛፍ፣ ጫፎቹን ችምችም ካለው ቅጠል በላይ ከፍ በማድረግ፣ ከእንግዲህ ራሱን በትዕቢት አያንጠራራም። ከእንግዲህ ውሃ በሚገባ ያገኘ ማንኛውም ዛፍ ወደዚህ ዐይነቱ ከፍታ አይደርስም። ሁሉም ከምድር በታች ወደ ጕድጓድ ከሚወርድ ሟች ጋር አብሮ እንዲሞት ተወስኖበታልና።”

15“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ወደ መቃብር
ዕብራይስጡ ሲኦል ይላል፤ እንዲሁም በ16 እና 17
በወረደበት ቀን ጥልቅ ምንጮችን ስለ እርሱ በሐዘን ሸፈንኋቸው፤ ወንዞቹን ገታሁ፤ ታላላቅ ፈሳሾችም ተቋረጡ። በእርሱም ምክንያት ሊባኖስን ጨለማ አለበስሁ፤ የደን ዛፎችም ሁሉ ደረቁ።
16ወደ ጕድጓድ ከሚሄዱት ጋር ወደ መቃብር ባወረድሁት ጊዜ ሲወድቅ በተሰማው ድምፅ አሕዛብ ደነገጡ። ከዚያም የዔድን ዛፎች ሁሉ፣ ምርጥና ልዩ የሆኑት የሊባኖስ ዛፎች፣ ውሃ የጠገቡትም ዛፎች ሁሉ ከምድር በታች ሆነው ተጽናኑ። 17ከአሕዛብ መካከል ከእርሱ ጋር ያበሩ፣ በጥላው ሥር የኖሩ፣ በሰይፍ ከሞቱት ጋር ለመቀላቀል ወደ መቃብር ወርደዋል።”

18“ ‘በዔድን ካሉት ዛፎች በውበትና በትልቅነት የሚወዳደርህ የትኛው ነው? ይሁን እንጂ አንተም እንደዚሁ ከዔድን ዛፎች ጋር ከመሬት በታች ትወርዳለህ፤ በሰይፍ ከተገደሉት፣ ካልተገረዙትም መካከል ትጋደማለህ።

“ ‘እንግዲህ ፈርዖንና ስፍር ቍጥር የሌለው ሕዝቡ የሚደርስባቸው ይህ ነው፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

Copyright information for AmhNASV