Genesis 20

አብርሃምና አቤሜሌክ

20፥1-18 ተጓ ምብ – ዘፍ 12፥10-20፤ 26፥1-11 1አብርሃም ከዚያ ተነሥቶ ወደ ኔጌብ አካባቢ ሄዶ በቃዴስና በሱር መካከል ሰፈረ፤ ለጥቂት ጊዜም በጌራራ ተቀመጠ። 2በዚያም አብርሃም ሚስቱን ሣራን፣ “እኅቴ ናት” ይል ነበር። ስለዚህ የጌራራ ንጉሥ አቢሜሌክ መልእክተኛ ልኮ ሣራን ወሰዳት።

3እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በአንድ ሌሊት በሕልም ወደ አቢሜሌክ መጥቶ፣ “እነሆ፤ በወሰድሃት ሴት ምክንያት ምዉት ነህ፤ እርሷ ባለ ባል ናት” አለው።

4አቢሜሌክም ገና አልደረሰባትም ነበርና እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ በደል ያልፈጸመውን ሕዝብ ታጠፋለህን? 5‘እኅቴ ናት’ ያለኝ ራሱ አይደለምን? ደግሞስ ራሷም ብትሆን፣ ‘ወንድሜ ነው’ አላለችምን? እኔ ይህን ያደረግሁት በቅን ልቦናና በንጹሕ እጅ ነው።”

6እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በሕልሙ እንዲህ አለው፤ “አንተ ይህን ያደረግኸው በቅን ልቦና መሆኑን ዐውቄአለሁ፤ በእኔም ላይ ኀጢአት እንዳትሠራ የጠበቅሁህና እንዳትነካትም ያደረግሁት ለዚሁ ነው። 7አሁንም ሚስቱን ለሰውየው መልስለት፤ ነቢይ ነውና ይጸልይልሃል፤ አንተም ትድናለህ፤ ባትመልስለት ግን አንተም ሆንህ የአንተ የሆነ ሁሉ እንደምትሞቱ ዕወቅ።”

8በማግስቱም ማለዳ፣ አቢሜሌክ ሹማምቱን ሁሉ ጠርቶ፣ የሆነውን ሁሉ ነገራቸው፤ እነርሱም ታላቅ ፍርሀት ዐደረባቸው። 9ከዚያም አቢሜሌክ አብርሃምን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ያደረግህብን ነገር ምንድን ነው? ምን በደልሁህና ነው በእኔና በግዛቴ ላይ እንዲህ ያለውን ታላቅ የጥፋት መዘዝ ያመጣህብን? በእውነቱ መደረግ የማይገባውን ነው ያደረግህብን።” 10ከዚያም አቢሜሌክ፣ “ለመሆኑ ይህን ያደረግህበት ምክንያት ምንድን ነው?” ሲል አብርሃምን ጠየቀው።

11አብርሃምም አቢሜሌክን እንዲህ አለው፤ “እዚህ ቦታ ፈሪሀ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አለመኖሩን ተገነዘብሁ፤ ሰዎቹም ለሚስቴ ሲሉ ይገድሉኛል ብዬ ሠጋሁ፤ 12ደግሞም እኮ በርግጥ እኅቴ ናት፤ ከአንድ እናት ባንወለድም በአባት አንድ ነን፤ ኋላም አገባኋት። 13እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አዝዞኝ ከአባቴ ቤት ወጥቼ በየአገሩ ስዞር፣ ‘ለእኔ ያለሽን ፍቅር በዚህ ግለጭልኝ፤ በየደረስንበት ስፍራ ሁሉ “እርሱ ወንድሜ ነው” በዪ’ ብያት ነበር።”

14ከዚያም አቢሜሌክ፣ በጎችና የቀንድ ከብቶች፣ ወንድና ሴት አገልጋዮችን ለአብርሃም ሰጠው፤ ሚስቱን ሣራንም መለሰለት። 15አቢሜሌክም አብርሃምን፣ “እነሆ፤ አገሬ አገርህ ናት፤ በፈቀድህበት ስፍራ መኖር ትችላለህ” አለው።

16ሣራንም፣ “እነሆ፤ ለወንድምሽ ለአብርሃም አንድ ሺሕ ጥሬ ብር
11.5 ኪሎ ግራም ገደማ ይሆናል።
እሰጠዋለሁ፤ ይህም በአንቺ ላይ ለተፈጸመው በደል ካሣ እንዲሆንና አብረውሽ ያሉ ሁሉ እንዲያውቁት ነው፤ በዚህም ንጽሕናሽ ይረጋገጣል” አላት።

17ከዚያም አብርሃም ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጸለየ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) አቢሜሌክን፣ ሚስቱንና ሴት አገልጋዮቹን ፈወሳቸው፤ እንደ ገናም ልጅ ለመውለድ በቁ። 18እግዚአብሔር (ያህዌ) በአብርሃም ሚስት በሣራ ምክንያት፣ በአቢሜሌክ ቤት የሚገኙትን ሴቶች ማሕፀናቸውን ሁሉ ዘግቶ ነበርና።

Copyright information for AmhNASV