Isaiah 60

የጽዮን ክብር

1“ብርሃንሽ መጥቷልና ተነሺ አብሪ፤
የእግዚአብሔርም ክብር ወጥቶልሻል።
2እነሆ፤ ጨለማ ምድርን፣
ድቅድቅ ጨለማም ሕዝቦችን ይሸፍናል፤
ነገር ግን እግዚአብሔር ወጥቶልሻል፤
ክብሩንም ይገልጥልሻል።
3ሕዝቦች ወደ ብርሃንሽ፣
ነገሥታትም ወደ ንጋትሽ ጸዳል ይመጣሉ።

4“ቀና በዪ፤ ዙሪያሽን ተመልከቺ፤
ሁሉም ተሰብስበው ወደ አንቺ ይመጣሉ፤
ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ፣
ሴቶች ልጆችሽም በዕቅፍ ወደ አንቺ ይመጣሉ።
5ከዚያም ታያለሽ፤ ታብረቀርቂያለሽ፤
ልብሽ ይዘልላል፤ በደስታም ይሞላል።
በባሕሮች ያለው ሀብት ወደ አንቺ ይመጣል፤
የነገሥታትም ብልጽግና የአንቺ ይሆናል።
6የግመል መንጋ፣
የምድያምና የጌፌር ግልገል ግመሎች
ምድርሽን ይሞላሉ፤
ወርቅና ዕጣን ይዘው፣
የእግዚአብሔርን ምስጋና እያወጁ፣
ሁሉም ከሳባ ይመጣሉ።
7የቄዳር የበግ መንጋ ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባል፤
የነባዮት አውራ በጎች ያገለግሉሻል።
እነዚህም በመሠዊያዬ ላይ ተቀባይነት የሚኖራቸው መሥዋዕቶች ይሆናሉ፤
እኔም የክብር መቅደሴን ግርማ አጐናጽፈዋለሁ።

8“ርግቦች ወደ ጐጇቸው እንደሚበርሩ፣
እንደ ደመና የሚጓዙ እነዚህ እነማን ናቸው?
9በርግጥ ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉ፤
እርሱ ክብሩን ስላጐናጸፈሽ፣
ለእስራኤል ቅዱስ፣
ለእግዚአብሔር አምላክሽ ክብር፣
ከሩቅ ወንዶች ልጆችሽን፣
ከነብራቸውና ከነወርቃቸው ለማምጣት፣
የተርሴስ መርከቦች
ወይም፣ የንግድ መርከቦች
ቀድመው ይወጣሉ።


10“ባዕዳን ቅጥሮችሽን ይሠራሉ፤
ነገሥታቶቻቸው ያገለግሉሻል፤
በቍጣዬ ብመታሽም፣
ርኅራኄዬን በፍቅር አሳይሻለሁ።
11በሮችሽ ምንጊዜም የተከፈቱ ይሆናሉ፤
ቀንም ሆነ ሌሊት ከቶ አይዘጉም፤
ይህም ሰዎች የመንግሥታትን ብልጽግና ወደ አንቺ እንዲያመጡ፣
ነገሥታታቸውም በድል ወደ አንቺ እንዲገቡ ነው።
12ለአንቺ የማይገዛ ሕዝብና መንግሥት ይጠፋል፤
ፈጽሞም ይደመሰሳል።

13“የመቅደሴን ቦታ ለማስጌጥ፣
የሊባኖስ ክብር፣
ጥዱ፣ አስታውና ባርሰነቱ በአንድነት ወደ አንቺ ይመጣሉ፤
እግሬ የሚያርፍበትንም ስፍራ አከብራለሁ።
14የአስጨናቂዎችሽ ወንዶች ልጆች እየሰገዱ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤
የናቁሽም ሁሉ እግርሽ ላይ ይደፋሉ፤
የእግዚአብሔር ከተማ፣
የእስራኤል ቅዱስ ገንዘብ የሆንሽው ጽዮን ብለው ይጠሩሻል።

15“የተተውሽና የተጠላሽ፣
ማንም ሰው የማያልፍብሽ ብትሆኝም እንኳ፣
እኔ የዘላለም ትምክሕት፣
የትውልድም ሁሉ ደስታ አደርግሻለሁ።
16የመንግሥታትን ወተት ትጠጪያለሽ፤
የነገሥታትንም ጡት ትጠቢያለሽ፤
ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አዳኝሽ፣
ቤዛሽም እኔ የያዕቆብ ኀያል እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ።
17በናስ ፈንታ ወርቅ፣
በብረትም ፈንታ ብር አመጣልሻለሁ።
ሰላምን ገዥሽ፣
ጽድቅንም አለቃሽ አደርጋለሁ።
18ከእንግዲህ በምድርሽ ሁከት፣
በጠረፎችሽም ጥፋትና መፈራረስ አይሰማም፤
ነገር ግን ቅጥሮችሽን ድነት፣
በሮችሽንም ምስጋና ብለሽ ትጠሪያቸዋለሽ።
19ከእንግዲህ በቀን የፀሓይ ብርሃን አያስፈልግሽም፤
በሌሊትም የጨረቃ ብርሃን አያበራልሽም፤
እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃን፣
አምላክሽም ክብርሽ ይሆናልና።
20ፀሓይሽ ከእንግዲህ አትጠልቅም፤
ጨረቃሽም ብርሃን መስጠቷን አታቋርጥም፤
እግዚአብሔር የዘላለም ብርሃንሽ ይሆናል፤
የሐዘንሽም ቀን ያከትማል።
21ሕዝብሽም ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤
ምድሪቱንም ለዘላለም ይወርሳሉ፤
ለክብሬ መግለጫ ይሆኑ ዘንድ፣
የእጆቼ ሥራ፣
እኔ የተከልኋቸው ቍጥቋጦች ናቸው።
22ከአንቺ ታናሽ የሆነው ሺሕ፣
ከሁሉም የመጨረሻው ታናሽ ኀያል መንግሥት ይሆናል፤
እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤
ጊዜውም ሲደርስ ይህን በፍጥነት አደርጋለሁ።”
Copyright information for AmhNASV