Job 11

ሶፋር

1ነዕማታዊው ሶፋር እንዲህ ሲል መለሰ፤

2“ይህ ሁሉ ቃል መልስ ማግኘት አይገባውምን?
ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ እውነተኛ ይቈጠርን?
3በውኑ የአንተ መዘላበድ ሰውን ዝም ያሰኛልን?
ስታፌዝስ የሚገሥጽህ የለም?
4እግዚአብሔርንም፣ ‘ትምህርቴ የጠራ፣
በዐይንህም ፊት የጸዳሁ ነኝ’ ትለዋለህ።
5ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ!
ከንፈሩንም በአንተ ላይ ቢከፍት!
6እውነተኛ ጥበብ ባለ ብዙ ፈርጅ ናትና፣
የጥበብንም ምስጢር ምነው በገለጠልህ!
እግዚአብሔር ለኀጢአትህ የሚገባውን እንዳላስከፈለህ ባወቅህ ነበር።

7“የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምስጢር ልትለካ ትችላለህን?
ወይስ ሁሉን የሚችለውን አምላክ መርምረህ ትደርስበታለህን?
8ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
ከሲኦልም
ወይም ከመቃብር
ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ?
9መጠኑ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፤
ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል።

10“እርሱ ተከታትሎ መጥቶ በግዞት ቢያስቀምጥህ፣
የፍርድ ሸንጎም ቢሰበስብ፣ ማን ሊከለክለው ይችላል?
11በእውነት እርሱ ሸፍጠኞችን ያውቃል፣
ክፋት ሲሠራም ልብ ይላል።
12ጅል ሰው ጥበበኛ ከሚሆን ይልቅ፣
የሜዳ አህያ ሰው ሆኖ ቢወለድ ይቀላል።
ወይም የዱር አህያ ለማዳ ሆኖ ሊወለድ ይችላል


13“ነገር ግን ልብህን ብትሰጠው፣
እጅህንም ወደ እርሱ ብትዘረጋ፣
14በእጅህ ያለውን ኀጢአት ብታርቅ፣
ክፋትም በድንኳንህ እንዳይኖር ብታደርግ፣
15በዚያን ጊዜ ሳታፍር ቀና ትላለህ፤
ያለ ፍርሀት ጸንተህ ትቆማለህ፤
16መከራህን ትረሳለህ፤
ዐልፎ እንደ ሄደ ጐርፍም ታስበዋለህ።
17ሕይወትህ ከቀትር ይልቅ ያበራል፤
ጨለማውም እንደ ንጋት ይሆናል።
18ተስፋ ስላለ ተደላድለህ ትቀመጣለህ፤
ዙሪያህን ትመለከታለህ፣ በሰላምም ታርፋለህ።
19ያለ አንዳች ሥጋት ትተኛለህ፤
ብዙ ሰዎችም ደጅ ይጠኑሃል።
20የክፉዎች ዐይን ግን ትጨልማለች፤
ማምለጫም አያገኙም፤
ተስፋቸውም ሞት ብቻ ነው።”
Copyright information for AmhNASV