Job 28

1“የብር ማዕድን የሚወጣበት፣
ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ።
2ብረት ከመሬት ውስጥ ይገኛል፤
መዳብም ከማዕድን ድንጋይ ቀልጦ ይወጣል።
3ሰው፣ እስከ ጨለማ መጨረሻ ይዘልቃል፤
ከድቅድቅ ጨለማ የማዕድን ድንጋይ ለማግኘት፣
እስከ ውስጠኛው ዋሻ ገብቶ ይፈልጋል።
4የሰው እግር ረግጦት በማያውቅበት ስፍራ፣
ከሰዎች መኖሪያ ርቆ መውረጃ ጕድጓድ ይቈፍራል፤
ሰው በሌለበት ቦታ ይንጠላጠላል፤ ይወዛወዛል።
5ከላይዋ ምግብን የምታስገኝ ምድር፣
ከታች በእሳት እንደሚሆን ትለዋወጣለች።
6ሰንፔር
በዚህና በ16 ላይ፣ ላፒስ ላዙሊ
ከዐለቷ ይወጣል፤
ከዐፈሯም የወርቅ አንኳር ይገኛል።
7ያን መንገድ ጭልፊት አያውቀውም፤
የአሞራም ዐይን አላየውም፣
8ኵሩ አራዊት አልረገጡትም፤
አንበሳም በዚያ አላለፈም።
9ሰው እጁን በቡላድ ድንጋይ ላይ ያነሣል፤
ተራሮችንም ከሥር ይገለብጣል።
10በድንጋይ ውስጥ መተላለፊያ ያበጃል፤
ዐይኖቹም የከበሩ ነገሮችን ሁሉ ያያሉ።
11የወንዞችን ምንጭ ይበረብራል፤
የሰብዓ ሊቃናት ትርጕምና ቩልጌት ከዚህ ጋር ይስማማል፤ ዕብራይስጡ ግን ይገድባል ይላል።

የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል።

12“ነገር ግን ጥበብ ከወዴት ትገኛለች?
ማስተዋልስ መኖሪያዋ የት ነው?
13ሰው ዋጋዋን አያውቅም፤
በሕያዋንም ምድር አትገኝም።
14ውቅያኖስ፣ ‘በእኔ ውስጥ የለችም’ ይላል፤
ባሕርም፣ ‘በእኔ ዘንድ አይደለችም’ ይላል።
15ንጹሕ ወርቅ ሊገዛት አይችልም፤
ዋጋዋም በብር አይመዘንም።
16በኦፊር ወርቅ፣
በከበረም መረግድና በሰንፔር አትገመትም።
17ወርቅም ብርሌም አይወዳደሯትም፤
በወርቅ ጌጥም አትለወጥም።
18ዛጐልና አልማዝ ከቍጥር አይገቡም፤
የጥበብ ዋጋ ከቀይ ዕንቍም ይበልጣል።
19የኢትዮጵያ ቶጳዝዮን ሊስተካከላት አይችልም፤
ዋጋዋም በንጹሕ ወርቅ አይተመንም።

20“ታዲያ፣ ጥበብ ከወዴት ትመጣለች?
ማስተዋልስ የት ትገኛለች?
21ከሕያዋን ፍጥረታት ዐይን ሁሉ ተሰውራለች፤
ከሰማይ ወፎችም ተሸሽጋለች።
22ጥፋትና
ዕብራይስጡ፣ አባዶን ይላል።
ሞት፣
‘ወሬዋን ብቻ ሰማን’ ይላሉ።
23ወደ እርሷ የሚወስደውን መንገድ የሚረዳ፣
መኖሪያዋንም የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤
24እርሱ የምድርን ዳርቻ ይመለከታልና፤
ከሰማይ በታች ያለውንም ሁሉ ያያል።
25ለነፋስ ኀይልን በሰጠ ጊዜ፣
የውሆችን መጠን በለካ ጊዜ፣
26ለዝናብ ሥርዐትን፣
ለነጐድጓድም መንገድን ባበጀ ጊዜ፣
27በዚያን ጊዜ ጥበብን ተመለከታት፤ ገመገማትም፤
አጸናት፤ መረመራትም።
28ከዚያም ሰውን፣
‘እግዚአብሔርን መፍራት ጥበብ ነው፤
ከክፋትም መራቅ ማስተዋል ነው’ አለው።”
Copyright information for AmhNASV