Lamentations 4

א አሌፍ

ይህ ምዕራፍ፣ ጥቅሶቹ ተከታታይ ፊደላት ባሉት የዕብራይስጥ ሆህያት የሚጀምር ቃል ወይም ዐረፍተ ነገር ያለው ግጥም ነው።
1ወርቁ እንዴት ደበሰ!
ንጹሑስ ወርቅ እንዴት ተለወጠ!
የከበሩ ድንጋዮች፣
በየመንገዱ ዳር ተበታትነዋል።
ב ቤት

2እንደ ወርቅ ይቈጠሩ የነበሩ፣
የከበሩ የጽዮን ወንዶች ልጆች፣
የሸክላ ሠሪ እጅ እንደ ሠራው፣
እንዴት አሁን እንደ ሸክላ ዕቃ ሆኑ!
ג ጊሜል

3ቀበሮዎች እንኳን ግልገሎቻቸውን ለማጥባት፣
ጡታቸውን ይሰጣሉ፤
ሕዝቤ ግን በምድረ በዳ እንዳሉ ሰጎኖች፣
ጨካኞች ሆኑ።
ד ዳሌት

4ከውሃ ጥም የተነሣ፣
የሕፃናት ምላስ ከላንቃቸው ጋር ተጣበቀ፤
ልጆቹ ምግብ ለመኑ፤
ነገር ግን ማንም አልሰጣቸውም።
ה ሄ

5ምርጥ ምግብ ይበሉ የነበሩ፣
ተቸግረው በየመንገዱ ላይ ተንከራተቱ፤
ሐምራዊ ግምጃ ለብሰው ያደጉ፣
አሁን በዐመድ ክምር ላይ ተኙ።
ו ዋው

6በሕዝቤ ላይ የደረሰው ቅጣት፣
የማንም እጅ ሳይረዳት፣
በድንገት ከተገለበጠችው፣
ሰዶም ላይ ከደረሰው ቅጣት ይልቅ ታላቅ ነው።
ז ዛይን

7መሳፍንታቸው ከበረዶ ይልቅ ብሩህ፣
ከወተትም ይልቅ ነጭ ነበሩ፤
ሰውነታቸው ከቀይ ዕንየቀላ፣
መልካቸውም እንደ ሰንፌር
ወይም ላፒስ ላዙሊ
ነበር።
ח ኼት

8አሁን ግን ከጥላሸት ይልቅ ጠቍረዋል፤
በመንገድም የሚያውቃቸው የለም፤
ቈዳቸው ከዐጥንታቸው ጋር ተጣብቋል፤
እንደ ዕንጨትም ደርቀዋል።
ט ቴት

9በራብ ከሚሞቱት ይልቅ፣
በሰይፍ የተገደሉት ይሻላሉ፤
ምግብ በሜዳ ላይ ካለማግኘታቸው የተነሣ፣
በራብ ደርቀው ያልቃሉ።
י ዮድ

10ሕዝቤ ባለቀበት ጊዜ፣
ምግብ እንዲሆኗቸው፣
ርኅሩኆቹ ሴቶች በገዛ እጆቻቸው፣
ልጆቻቸውን ቀቀሉ።
כ ካፍ

11 እግዚአብሔር ለመቅሠፍቱ መውጫ በር ከፈተ፤
ጽኑ ቍጣውን አፈሰሰ፤
መሠረቷን እንዲበላ፣
በጽዮን እሳት ለኰሰ።
ל ላሜድ

12ጠላቶችም ሆኑ ወራሪዎች፣
የኢየሩሳሌምን በሮች ጥሰው ይገባሉ ብለው፣
የምድር ነገሥታት፣
ወይም ከዓለም ሕዝብ አንዳቸውም አላመኑም።
מ ሜም

13ይህ ግን ከነቢያት ኀጢአት፣
ከካህናቷም መተላለፍ የተነሣ ሆኗል፤
በውስጧ፣
የጻድቃንን ደም አፍስሰዋልና።
נ ኑን

14እንደ ታወሩ ሰዎች፣
በየመንገዱ ላይ ይደናበራሉ፤
ማንም ሰው ደፍሮ ልብሳቸውን መንካት እስከማይችል ድረስ፣
በደም እጅግ ረክሰዋል።
ס ሳሜክ

15ሰዎች “ሂዱ! እናንት ርኩሳን!” ብለው ይጮኹባቸዋል፤
“ወግዱ! ወግዱ! አትንኩ!” ይሏቸዋል፤
ሸሽተው በሚቅበዘበዙበትም ጊዜ፣
በአሕዛብ መካከል ያሉ ሰዎች፣
“ከእንግዲህ በዚህ መቀመጥ አይገባቸውም!” ይላሉ።
ע ዐዪን

16 እግዚአብሔር ራሱ በትኗቸዋል፤
ከእንግዲህ ወዲያ አይጠብቃቸውም፤
ካህናቱ አልተከበሩም፤
ሽማግሌዎቹም ከበሬታ አላገኙም።
פ ፌ

17ከሁሉም በላይ በከንቱ ርዳታን ስንጠባበቅ፣
ዐይኖቻችን ደከሙ፤
ከግንብ ማማችን ላይ ሆነን፣
ሊያድን ከማይችል ሕዝብ ርዳታ ጠበቅን።
צ ጻዲ

18ሰዎች እግር እግራችንን ተከታተሉን፤
ስለዚህ በመንገዳችን መሄድ አልቻልንም፤
መጨረሻችን ቀርቧል፤ ቀኖቻችንም ተቈጥረዋል፤
ፍጻሜያችን መጥቷልና።
ק ቆፍ

19ከሰማይ ንስሮች ይልቅ፣
ጠላቶቻችን ፈጣኖች ናቸው፤
በተራሮች ላይ አሳደዱን፤
በምድረ በዳም ሸመቁብን።
ר ሬሽ

20 በእግዚአብሔር የተቀባው፣ የሕይወታችን እስትንፋስ፣
በወጥመዳቸው ተያዘ፤
በጥላው ሥር፣
በአሕዛብ መካከል እንኖራለን ብለን አስበን ነበር።
ש ሲን እና ሺን

21አንቺ በዖፅ ምድር የምትኖሪ፣
የኤዶምያስ ሴት ልጅ ሆይ፤ ደስ ይበልሽ፤ ሐሤትም አድርጊ፤
ነገር ግን ለአንቺም ደግሞ ጽዋው ይደርስሻል፤
ትሰክሪያለሽ፤ ዕርቃንሽንም ትጋለጫለሽ።
ת ታው

22የጽዮን ልጅ ሆይ፤ ቅጣትሽ ያበቃል፤
እርሱም የስደትሽን ዘመን አያራዝምም፤
ነገር ግን አንቺ የኤዶምያስ ልጅ ሆይ፤
ኀጢአትሽን ይቀጣል፤
ክፋትሽንም ይፋ ያወጣል።
Copyright information for AmhNASV