Psalms 111

ለመለኮቱ ባሕርያት የቀረበ ጸሎት

1ሃሌ ሉያ።

በቅኖች ሸንጎ፣ በጉባኤም መካከል፣
ለእግዚአብሔር በፍጹም ልቤ ምስጋና አቀርባለሁ።

2 የእግዚአብሔር ሥራ ታላቅ ናት፤
ደስ የሚሰኙባትም ሁሉ ያውጠነጥኗታል።
3ሥራው ባለ ክብርና ባለ ግርማ ነው፤
ጽድቁም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
4ድንቅ ሥራው ሲታወስ እንዲኖር አደረገ፤
እግዚአብሔር ቸር፣ ርኅሩኅም ነው።
5ለሚፈሩት ምግብን ይሰጣል፤
ኪዳኑንም ለዘላለም ያስባል።
6ለሕዝቡ የአሕዛብን ርስት በመስጠት፣
የአሠራሩን ብርታት አሳይቷል።
7የእጁ ሥራ እውነተኛና ቅን ነው፤
ሥርዐቱም ሁሉ የታመነ ነው፤
8ከዘላለም እስከ ለዘላለም የጸና ነው፤
በእውነትና በቅንነትም የተሠራ ነው።
9ለሕዝቡ መዳንን ሰደደ፤
ኪዳኑንም ለዘላለም አዘዘ፤
ስሙም የተቀደሰና የተፈራ ነው።

10 እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው፤
ትእዛዙንም የሚፈጽሙ ጥሩ ማስተዋል አላቸው፤
ምስጋናውም ለዘላለም ይኖራል።
Copyright information for AmhNASV