Psalms 12

ከክፉ ዓለም ለመዳን የቀረበ ጸሎት

ለመዘምራን አለቃ፤ በስምንተኛው ቅኝት የሚዘመር፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ደግ ሰው የለምና አንተው ድረስልኝ!
ከሰዎችም መካከል አንድ ታማኝ አይገኝም።
2እርስ በርሳቸው ውሸት ይነጋገራሉ፤
በሽንገላ ከንፈርና በሁለት ልብ ይናገራሉ።

3ሸንጋዩን ከንፈር ሁሉ፣
ነገር የምታበዛውንም ምላስ እግዚአብሔር ያጥፋ!
4እነዚህም፣ “በአንደበታችን እንረታለን፤
ከንፈራችን የእኛ ነው፤
ወይም ከንፈራችን ማረሻ ምላጫችን ነው
ጌታችንስ ማነው?”
የሚሉ ናቸው።

5 እግዚአብሔር፣ “ስለ ድኾች መከራ፣
ስለ ችግረኞችም ጩኸት፣
አሁን እነሣለሁ፤
በናፈቁትም ሰላም አኖራቸዋለሁ” ይላል።
6 የእግዚአብሔር ቃል የጠራ ቃል ነው፤
ሰባት ጊዜ እንደ ተጣራ፣
በምድር ላይ በከውር እንደ ተፈተነ ብር ነው።

7 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ትጠብቀናለህ፤
ከዚህም ትውልድ ለዘላለም ትከልለናለህ።
8በሰዎች ዘንድ ክፋት ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ፣
ዐመፀኞች በየአቅጣጫው በዛቻ ይዞራሉ።
Copyright information for AmhNASV