Psalms 54

ለፍትሕ አምላክ የቀረበ አቤቱታ

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ ዜፋውያን ወደ ሳኦል መጥተው፣ “ዳዊት በእኛ ዘንድ ተደብቋል” ባሉት ጊዜ፤ የዳዊት ትምህርት
ርእሱ የሥነ ጽሑፉን ቅርጽ ወይም የመዝሙሩን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።

1እግዚአብሔር ሆይ፤ በስምህ አድነኝ፤
በኀይልህም ፍረድልኝ።
2እግዚአብሔር ሆይ፤ ጸሎቴን ስማልኝ፤
የአፌንም ቃል አድምጥ።

3ባዕዳን ተነሥተውብኛልና፤
ግፈኞች ነፍሴን ሽተዋታል፤
እግዚአብሔርንም ከምንም አልቈጠሩም። ሴላ

4እነሆ፤ እግዚአብሔር ረዳቴ ነው፤
ጌታም ደግፎ ይይዘኛል።

5የገዛ ክፋታቸው በሚያደቡብኝ ላይ ይመለስባቸው፤
በቃልህ ታማኝ ነህና አጥፋቸው።

6በበጎ ፈቃድ መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ መልካም ነውና፣
ለስምህ ምስጋና አቀርባለሁ፤
7ከመከራ ሁሉ ታድጎኛልና፤
ዐይኔም የጠላቶቼን ውድቀት ለማየት በቅቷል።
Copyright information for AmhNASV