Revelation of John 14

በጉና መቶ አርባ አራቱ ሺሕ ሰዎች

1ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆ፤ በጉ በጽዮን ተራራ ላይ ቆሞ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የእርሱ ስምና የአባቱ ስም በግንባራቸው ላይ የተጻፈባቸው መቶ አርባ አራቱ ሺሕ ሰዎች ነበሩ። 2ከሰማይ እንደ ብዙ ውሃ ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ የመሰለ ድምፅ ሰማሁ፤ የሰማሁት ድምፅ በገና ደርዳሪዎች እንደሚደረድሩት ዐይነት ነበረ። 3እነርሱም በዙፋኑ ፊት፣ በአራቱ ሕያዋን ፍጡራንና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ መዝሙር ዘመሩ። ከምድር ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራቱ ሺሕ ሰዎች በስተቀር መዝሙሩን ማንም ሊማረው አልቻለም። 4እነዚህ ራሳቸውን በሴቶች ያላረከሱት ናቸው፤ ራሳቸውን በንጽሕና ጠብቀዋልና። በጉ ወደሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል፤ ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ ናቸው። 5በአፋቸው ምንም ዐይነት ውሸት አልተገኘም፤ ነቀፋም የለባቸውም።

ሦስቱ መላእክት

6ከዚያም ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበርር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር፤ 7በታላቅ ድምፅም፣ “እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሷል፤ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ” አለ።

8ሌላም ሁለተኛ መልአክ፣ “ሕዝቦች ሁሉ፣ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ እንዲጠጡ ያደረገች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!” እያለ ተከተለው።

9ሦስተኛውም መልአክ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ ተከተላቸው፤ “ማንም ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ፣ ምልክቱንም በግንባሩ ወይም በእጁ ላይ የሚቀበል ቢኖር፣ 10እርሱ ደግሞ ምንም ነገር ሳይቀላቀልበት በቍጣው ጽዋ ውስጥ የተሞላውን የእግዚአብሔርን ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል። በቅዱሳን መላእክትና በበጉ ፊትም በእሳትና በዲን ይሠቃያል። 11የሥቃያቸውም ጢስ ከዘላለም እስከ ዘላለም ወደ ላይ ይወጣል። ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ ወይም የስሙንም ምልክት የሚቀበሉ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።” 12የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ ቅዱሳን የሚታወቁት በዚህ ነው።

13ከዚያም፣ “ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ ሆነው የሚሞቱ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ” የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰማሁ። መንፈስም፣ “አዎ፣ ሥራቸው ስለሚከተላቸው ከድካማቸው ያርፋሉ” ይላል።

የምድር መከር ጊዜ

14አየሁም፤ እነሆ፤ በፊቴ ነጭ ደመና ነበረ፤ በደመናውም ላይ፣ “የሰውን ልጅ የሚመስል” ተቀምጦ ነበር፤ እርሱም በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል ደፍቶ፣ በእጁም ስለታም ማጭድ ይዞ ነበር። 15ሌላም መልአክ ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው፣ “የዐጨዳው ሰዓት ስለ ደረሰ፣ ማጭድህን ይዘህ ዕጨድ፤ የምድር መከር ደርሷልና” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ። 16ስለዚህ በደመናው ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደ፤ ምድርም ታጨደች።

17ሌላም መልአክ በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፤ እርሱም እንዲሁ ስለታም ማጭድ ነበረው፤ 18በእሳት ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ የያዘውን፣ “ዘለላው ስለ በሰለ፣ ስለታም ማጭድህን ያዝና በምድር ላይ ያሉትን የወይን ዘለላዎች ሰብስብ” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ። 19መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ሰደደ፤ የምድርን የወይን ዘለላዎች ሰብስቦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር የቍጣ ወይን መጭመቂያ ጣላቸው። 20ወይኑም ከከተማው ውጭ በወይን መጭመቂያ ውስጥ ተረገጠ፤ ከፍታው እስከ ፈረስ ልጓም የሚደርስ፣ ርዝመቱ ሦስት መቶ ኪሎ ሜትር
ግሪኩ አንድ ሺሕ ስድስት መቶ ምዕራፍ ይላል።
ያህል ደም ከመጭመቂያው ወጣ።

Copyright information for AmhNASV