1 Kings 15

የይሁዳ ንጉሥ አብያ

15፥1-2፡7-8 ተጓ ምብ – 2ዜና 13፥1-2፡22–14፥1 1የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያ
በዚህ ስፍራና በ7 እና 8 ላይ እንዳንድ የዕብራይስጥና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ትርጕሞች ግን፤ አቢጃም ይላሉ
በይሁዳ ነገሠ፤
2በኢየሩሳሌም ሆኖ ሦስት ዓመት ገዛ፤ እናቱ መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።

3እርሱም አባቱ ከእርሱ በፊት የሠራውን ኀጢአት ሁሉ ሠራ፤ እንደ አባቱ እንደ ዳዊትም በፍጹም ልቡ በታማኝነት ለእግዚአብሔር አልተገዛም። 4ነገር ግን ከእርሱ ቀጥሎ እንዲነግሥና ኢየሩሳሌምን እንዲያጸናት፣ አምላክ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው። 5ዳዊት በኬጢያዊው በኦርዮ ላይ ካደረሰው በደል በቀር፣ በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነውን ነገር አድርጓል፤ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ፈቀቅ ያለበት ጊዜ አልነበረም።

6አብያም
አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ከዚህ ጋር ይስማማሉ አንዳንድ የዕብራይስጥና የሱርስት ትርጕሞች ግን፣ አቢጃም ይላሉ
በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በሮብዓምና በኢዮርብዓም መካከል ጦርነት ነበር።
7ሌላው አብያ በዘመኑ የፈጸመውና ያደረገው ሁሉ፣ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከልም ጦርነት ነበር። 8አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። ልጁም አሳ በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የይሁዳ ንጉሥ አሳ

15፥9-22 ተጓ ምብ – 2ዜና 14፥2-3፤ 15፥16–16፥6 15፥23-24 ተጓ ምብ – 2ዜና 16፥11–17፥1 9የእስራኤል ንጉሥ ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያኛው ዓመት፣ አሳ የይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ 10በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ አያቱ መዓካ ትባላለች፤ እርሷም የአቤሴሎም ልጅ ነበረች።

11አሳ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ። 12የቤተ ጣዖት ወንደቃዎችን ከምድሪቱ አባረረ፤ አባቶቹ የሠሯቸውን ጣዖታት ሁሉ አስወገደ። 13አስጸያፊውን የአሼራ ምስል ዐምድ በማቆሟ፣ አያቱን መዓካን ከእቴጌነቷ ሻራት፤ ጣዖቷንም ሰባብሮ በቄድሮን ሸለቆ አቃጠለው። 14አሳ የማምለኪያ ኰረብታዎችን ፈጽሞ ባያስወግድም እንኳ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ፣ ልቡ ለእግዚአብሔር የተገዛ ነበር። 15አባቱና እርሱ ለእግዚአብሔር የቀደሱትን ብርና ወርቅ እንዲሁም ዕቃዎችን አምጥቶ ወደ እግዚአብሔር ቤት አስገባ።

16አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት፣ እርስ በርስ በመዋጋት ነበር። 17የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ይሁዳን ለመውጋት ወጣ፤ ከዚያም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሳ ግዛት ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ለመቈጣጠር ራማን ምሽግ አድርጎ ሠራት።

18አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት የቀረውን ብርና ወርቅ በሙሉ ወሰደ፤ ከዚያም በታማኝ ሹማምቱ እጅ በደማስቆ ይገዛ ለነበረው፣ ለጠብሪሞን ልጅ፣ የአዚን የልጅ ልጅ ለሆነው ለሶርያ ንጉሥ ለቤን ሀዳድ ላከው። 19እንዲህም አለ፤ “በአባቴና በአባትህ መካከል የስምምነት ውል እንደ ነበረ ሁሉ፣ አሁንም በእኔና በአንተ መካከል ይኑር። እነሆ፤ የብርና የወርቅ ገጸ በረከት ልኬልሃለሁ። አሁንም የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ወደ መጣበት እንዲመለስ፣ ሄደህ ከእርሱ ጋር ያደረግኸውን የስምምነት ውል አፍርስ።”

20ቤን ሃዳድም የንጉሥ አሳን ሐሳብ ተቀብሎ፣ የጦር አዛዦቹን በእስራኤል ከተሞች ላይ አዘመተ፤ ዒዮንን፣ ዳንን፣ አቤልቤት ማዕካን እንዲሁም ንፍታሌምን ጨምሮ ጌንሳሬጥን በሙሉ ድል አደረገ። 21ባኦስም ይህን ሲሰማ፣ በራማ የጀመረውን የምሽግ ሥራ አቁሞ ወደ ቴርሳ ተመለሰ። 22ንጉሥ አሳ አንድም ሰው እንዳይቀር በይሁዳ ሁሉ ዐዋጅ አስነገረ፤ ከዚያም ሕዝቡ ባኦስ በራማ አስቀምጦት የነበረውን ድንጋይና ዕንጨት አጋዘ፤ ንጉሡም በዚሁ ምጽጳንና በብንያም ውስጥ ጌባን ሠራ።

23በአሳ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ነገር በሙሉ፣ ያደረገውም ሁሉና የሠራቸውም ከተሞች በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፈው የሚገኙ አይደሉምን? ንጉሥ አሳ በሸመገለ ጊዜ ግን እግሮቹ ታመሙ። 24አሳ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በአባቱ በዳዊት ከተማ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮሣፍጥም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

የእስራኤል ንጉሥ ናዳብ

25በይሁዳ ንጉሥ በአሳ ዘመነ መንግሥት በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናዳብ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። 26እርሱም በአባቱ መንገድ በመሄድ፣ አባቱ የሠራውንና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመሥራት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

27ናዳብና መላው እስራኤል በፍልስጥኤም የምትገኘውን የገባቶንን ከተማ ከብበው ሳሉ፣ ከይሳኮር ነገድ የተወለደው የአኪያ ልጅ ባኦስ ዐምፆ በመነሣት ናዳብን በገባቶን ገደለው። 28ባኦስ ናዳብን የገደለውና በእግሩ ተተክቶ የነገሠው፣ የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት ነው።

29ወዲያውኑ እንደ ነገሠም የኢዮርብዓምን ቤተ ሰብ በሙሉ ፈጀ። እግዚአብሔር በሴሎናዊው ባሪያው በአኪያ በኩል እንደ ተናገረው፣ ከኢዮርብዓም ቤተ ሰብ አንድም ሰው በሕይወት ሳያስቀር፣ ሁሉንም አጠፋቸው፤ 30ይህም የሆነው ኢዮርብዓም በሠራው ኀጢአትና እስራኤልም እንዲሠሩ በማድረጉ ምክንያት፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔርን ለቍጣ በማነሣሣቱ ነው።

31ሌላው በናዳብ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው፣ እርሱም ያደረገው ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 32አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ ዘመነ መንግሥታቸውን ያሳለፉት እርስ በርስ በመዋጋት ነበር።

የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ

33የይሁዳ ንጉሥ አሳ በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በቴርሳ ከተማ፣ በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፤ ሃያ አራት ዓመትም ገዛ። 34በኢዮርብዓም መንገድ በመሄድና እስራኤልም እንዲሠሩ ያደረገውን ኀጢአት በመፈጸም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠራ።

Copyright information for AmhNASV