2 Chronicles 22

የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ

22፥1-6 ተጓ ምብ – 2ነገ 8፥25-29 22፥7-9 ተጓ ምብ – 2ነገ 9፥21-29 1ከዐረቦች ጋር ወደ ሰፈር የመጡት ወራሪዎች፣ ታላላቅ ወንድሞቹን ሁሉ ገድለዋቸው ስለ ነበር፣ የኢየሩሳሌም ሕዝብ የኢዮሆራምን የመጨረሻ ልጅ አካዝያስን በአባቱ ምትክ አነገሡት። ስለዚህ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ መግዛት ጀመረ። 2አካዝያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ ሁለት
አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናትና የሱርስቱ ቅጆች (እንዲሁም 2ነገ 8፥26 ይመ) ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ ዕብራይስጡ ግን አርባ አራት ይላል።
ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የዘንበሪ የልጅ ልጅ ነበረች።

3እናቱ ክፋትን እንዲያደርግ ትመክረው ስለ ነበር፣ እርሱም በአክዓብ ቤት መንገድ ሄደ። 4ከአባቱ ሞት በኋላ የአክዓብ ቤት አማካሪዎቹ በመሆን ወደ ጥፋት ስለ መሩት፣ የአክዓብ ቤት እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር አደረገ። 5እንዲሁም የእስራኤል ንጉሥ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን ለመውጋት ወደ ሬማት ገለዓድ በሄደ ጊዜ፣ የእነዚህኑ ሰዎች ምክር ተከትሎ ከኢዮራም ጋር አብሮት ሄደ፣ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቈሰሉት።

6ስለዚህ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር ባደረገው ጦርነት ሬማት
ጥቂት የዕብራይስጥ ቅጆች የሰብዓ ሊቃናት፣ የቩልጌትና የሱርስቱ ትርጕም (2ነገ 8፥29) ከዚህ ጋር ይስማማሉ አብዛኞቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ግን፣ አዛርያ ይላሉ።
ላይ ከደረሰበት ቍስል ለመዳን ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ።

የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በመቍሰሉም የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሆራም ልጅ አካዝያስ ሊጠይቀው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

7አካዝያስ ኢዮራምን ለመጠየቅ መሄዱን፣ እግዚአብሔር ለአካዝያስ መውደቅ ምክንያት አደረገው፤ አካዝያስ እንደ ደረሰም የናሜሲን ልጅ ኢዩን ለመቀበል ከኢዮራም ጋር ወጣ፤ ኢዩም የአክዓብን ቤት እንዲያጠፋ እግዚአብሔር የቀባው ሰው ነበር። 8ኢዩ በአክዓብ ቤት ላይ ፍርድ በሚፈጽምበት ጊዜ፣ አካዝያስን ያጅቡ የነበሩትን የይሁዳን መሳፍንትና የዘመዶቹን ወንዶች ልጆች አግኝቶ ገደላቸው። 9ከዚያም አካዝያስን ለመፈለግ ሄደ፤ የእርሱም ሰዎች አካዝያስን በሰማርያ ከተደበቀበት አግኝተው ያዙት፤ ወደ ኢዩም አምጥተው ገደሉት። “እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ የፈለገው የኢዮሣፍጥ ልጅ ነው” በማለት ቀበሩት። ስለዚህ ከአካዝያስ ቤት የመንግሥቱን ሥልጣን ይይዝ ዘንድ የሚችል ሰው አልነበረም።

ጎቶልያና ኢዮአስ

22፥10–23፥21 ተጓ ምብ – 2ነገ 11፥1-21 10የአካዝያስ እናት ጎቶልያ ልጇ መሞቱን ባየች ጊዜ፣ የይሁዳን ንጉሣውያን ቤተ ሰብ በሙሉ አጠፋች፤ 11የንጉሥ ኢዮሆራም ልጅ ዮሳቤት ግን፣ ከሚገደሉት መሳፍንት መካከል ኢዮአስን ደብቃ ወሰደችው፣ ከሞግዚቱም ጋር በእልፍኝ ሸሸገችው። የኢዮሆራም ልጅ የካህኑ የዮዳሄ ሚስት ዮሳቤት፣ የአካዝያስ እኅት በመሆኗ፣ ሕፃኑን የደበቀችው ጎቶልያ እንዳትገድለው ነበር። 12እርሱም ጎቶልያ ምድሪቱን በገዛችበት ጊዜ ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተደብቆ ስድስት ዓመት አብሯቸው ኖረ።

Copyright information for AmhNASV