2 Kings 16

የይሁዳ ንጉሥ አካዝ

16፥1-20 ተጓ ምብ – 2ዜና 28፥1-27 1የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በነገሠ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት፣ የይሁዳ ንጉሥ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ ነገሠ። 2አካዝ ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ዐሥራ ስድስት ዓመት ገዛ። አባቱ ዳዊት ያደረገውን መልካም ነገር በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት አላደረገም። 3እርሱም የእስራኤልን ነገሥታት መንገድ ተከተለ፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ፊት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን ርኩሰት ተከትሎ፣ ልጁን በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።
ወይም፣ ልጁን ገደለ
4እንዲሁም ኰረብታ ላይ ባሉ ማምለኪያ ስፍራዎች፣ በኰረብታ ዐናቶችና ቅጠሉ በተንሰራፋው ዛፍ ሥር ሁሉ ሠዋ፤ ዕጣንም አጤሰ።

5የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ለመውጋትና አካዝን ለመክበብ ወጡ፤ ይሁን እንጂ ሊያሸንፉት አልቻሉም። 6በዚያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶን የይሁዳን ሰዎች አሳድዶ፣ ኤላትን ወደ ሶርያ ግዛት መለሰ፤ ከዚያም ኤዶማውያን ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ በዚያ ይኖራሉ።

7ከዚህ የተነሣም አካዝ፣ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር፣ “እኔ አገልጋይህም ልጅህም ነኝ፤ ስለዚህ መጥተህ ከሚወጉኝ ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” ሲል መልእክተኞች ላከበት። 8አካዝም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤቶች የሚገኘውን ብርና ወርቅ አውጥቶ ለአሦር ንጉሥ ገጸ በረከት ላከለት። 9የአሦር ንጉሥም፣ የአካዝን ልመና በመቀበል፤ ደማስቆን አጥቅቶ ያዛት፤ ሕዝቧን ማርኮ ወደ ቂር አፈለሳቸው፤ ረአሶንንም ገደለው።

10ከዚያም ንጉሥ አካዝ የአሦርን ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶርን ለመገናኘት ወደ ደማስቆ ሄደ። በደማስቆም ያለውን መሠዊያ አይቶ፣ ንድፉን ከዝርዝር ጥናቱ ጋር ለካህኑ ለኦርያ ላከለት። 11ካህኑ ኦርያም ንጉሥ አካዝ ከደማስቆ በላከለት ዝርዝር ጥናት መሠረት መሠዊያ ሠራ፤ ንጉሡ አካዝ ከመመለሱም በፊት አጠናቀቀው። 12ንጉሡ ከደማስቆ ተመልሶ በመጣ ጊዜ፣ መሠዊያውን አየ፤ ቀርቦም በመሠዊያው ላይ ወጣ፤ 13ከዚያም የሚቃጠል መሥዋዕቱንና የእህል ቍርባኑን በመሠዊያው ላይ አቀረበ፤ የመጠጥ ቍርባኑን አፈሰሰ፤ የኅብረት መሥዋዕቱንም
በትውፊት፣ የሰላም መሥዋዕት
ደም በመሠዊያው ላይ ረጨ።
14በአዲሱ መሠዊያና በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መካከል፣ በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ የነበረውን የናስ መሠዊያ፣ ከቦታው አስነሥቶ ከአዲሱ መሠዊያ በስተ ሰሜን በኩል አኖረው።

15ከዚያም ንጉሥ አካዝ፣ ካህኑን ኦርያን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በዚህ በትልቁ አዲስ መሠዊያ ላይ የጧቱን የሚቃጠል መሥዋዕትና የማታውን የእህል ቍርባን፣ የንጉሡን የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን እንዲሁም የመላውን የአገሪቱን ሕዝብ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህልና የመጠጥ ቍርባናቸውን አቅርብ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ደምና የሌላውን መሥዋዕት ደም ሁሉ በመሠዊያው ላይ እርጨው፤ የናሱ መሠዊያ ግን እኔ መመሪያ ለመጠየቅ የምጠቀምበት ይሆናል።” 16ካህኑ ኦርያም ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።

17ንጉሡ አካዝም የጐንና የጐን ሳንቃዎቹን ነቅሎ ወሰደ፤ በተንቀሳቃሹ መቆሚያ ላይ ያሉትን የመታጠቢያ ሳሕኖች አስወገደ። የውሃ ማጠራቀሚያውን ክብ ገንዳ ከታች ተሸክመው ከያዙት ከዐሥራ ሁለቱ የናስ ቅርጽ ኮርማዎች ላይ አውርዶ በጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ አስቀመጠው። 18የአሦርንም ንጉሥ ለማስደሰት ሲል፣ በዕለተ ሰንበት ንጉሣዊ ዙፋን
የሰብዓ ሊቃናት መሥዋዕት ትርጕም፣ የዙፋኑ ሰሌዳ ይላል።
እንዲዘረጋበት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የተሠራውን ከፍ ያለ ስፍራና ነገሥታቱ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሚገቡበትን በውጭ ያለውን መግቢያ አነሣ።

19በአካዝ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን? 20አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ ከእነርሱ ጋር በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ሕዝቅያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

Copyright information for AmhNASV