2 Kings 7

1ኤልሳዕም፣ “እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በነገው ዕለት በዚሁ ሰዓት፣ በሰማርያ በር አንድ መስፈሪያ ማለፊያ ዱቄት በአንድ ሰቅል፣ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ይሸጣል’ ” አለ።

2ንጉሡ በክንዱ ላይ የተደገፈውም የጦር አለቃ፣ የእግዚአብሔርን ሰው፣ “እንዲያው ለመሆኑ፣ እግዚአብሔር የሰማያትን መስኮቶች ቢከፍት እንኳ ይህ ሊሆን ይችላልን?” ሲል ጠየቀው።

ኤልሳዕም፣ “ይህን አንተው ራስህ በዐይንህ ታየዋለህ፤ ይሁን እንጂ ከዚያ አንዳች አትቀምስም” አለው።

ከበባው ተወገደ

3በዚህ ጊዜ የሚያሠቅቅ የቈዳ በሽታ የያዛቸው አራት ሰዎች በከተማዪቱ መግቢያ በር አጠገብ ነበሩ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “እስክንሞት ድረስ በዚህ የምንቈየው ለምንድን ነው? 4ታዲያ፣ ‘ወደ ከተማዪቱ እንግባ ብንል’ በዚያም ራብ ስላለ እንሞታለን፤ በዚሁም ብንሆን ያው መሞታችን አይቀርም፤ ስለዚህ ወደ ሶርያውያኑ ሰፈር ዝም ብለን እንሂድ፤ ዝም ካሉን ሕይወታችን ትተርፋለች፤ ከገደሉንም ሞቶ መገላገል ነው።”

5ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ፤ ወደ ሰፈሩ ጥግ ሲደርሱም አንድም ሰው በዚያ አልነበረም። 6ይህ የሆነበትም ምክንያት፣ እግዚአብሔር የሠረገሎችንና የፈረሶችን እንዲሁም የብዙ ሰራዊት ድምፅ ሶርያውያን እንዲሰሙ አድርጎ ስለ ነበር ነው፤ እርስ በእርሳቸውም፣ “እነሆ፣ የእስራኤል ንጉሥ በእኛ ላይ አደጋ ለመጣል፣ የኬጢያውያንንና የግብፃውያንን ነገሥታት ቀጥሮ አምጥቶብናል” ተባባሉ። 7ከዚያም መሸትሸት ሲል ተነሥተው ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውን፣ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውንም አልወሰዱም ነፍሳቸውን ብቻ ለማዳን ሲሉ ሰፈሩን እንዲሁ እንዳለ ትተው ሄዱ።

8ለምጽ ያለባቸውም ሰዎች ወደ ሰፈሩ አጠገብ ከደረሱ በኋላ፣ ከድንኳኖቹ ወደ አንዱ ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም ብር፣ ወርቅና ልብስ ይዘው በመሄድ ደበቁት። ተመልሰው በመምጣትም ወደ ሌላው ድንኳን ገብተው ሌሎች ነገሮችን በመውሰድ እንደዚሁ ደበቁ።

9እርስ በርሳቸውም፣ “ያደረግነው ትክክል አይደለም፤ ዕለቱ የምሥራች ቀን ነው፤ እኛ ግን የራሳችን ብቻ አደረግነው፤ እስኪነጋም ከቈየን በደለኞች እንሆናለን፤ ስለዚህ ወደ ቤተ መንግሥት በፍጥነት ሄደን እንንገር” ተባባሉ።

10ስለዚህ ሄደው የከተማዪቱን መግቢያ በር ጠባቂዎች ጮኸው በመጥራት፣ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገባን፤ እዚያም ከታሰሩ ፈረሶችና አህዮች በቀር አንድም ሰው አልነበረም፤ የማንም ድምፅ አልተሰማም፤ ድንኳኖቹም እንዳሉ ናቸው” ብለው ነገሯቸው። 11የበሩ ጠባቂዎችም ይህንኑ አስተጋቡ፤ ዜናውም በቤተ መንግሥቱ ተሰማ።

12ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ለጦር አለቆቹ እንዲህ አላቸው፤ “ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ መራባችንን ስለሚያውቁ፣ ‘መቼም መውጣታቸው አይቀርም፤ ከዚያም ከነሕይወታቸው እንማርካቸዋለን፤ እኛም ሰተት ብለን ወደ ከተማዪቱ እንገባለን’ በማለት በገጠር ለመደበቅ ከሰፈራቸው ወጥተዋል።”

13ከጦር አለቆቹም አንዱ እንዲህ አለ፤ “ጥቂት ሰዎች በከተማዪቱ ውስጥ ከተረፉት ፈረሶች አምስቱን ይዘው ይሂዱ፤ ዕጣ ፈንታቸውም በዚህ ከቀሩት እስራኤላውያን ሁሉ ዕድል ጋር አንድ ነው፤ የሚጠብቃቸው ቢኖር በዚህ በሙሉ እንዳለቁት እስራኤላውያን መሆን ብቻ ነው፤ ስለዚህ እንላካቸውና የሆነውን እንይ።”

14ስለዚህ ሁለት ሠረገሎች ከነፈረሶቻቸው መረጡ፤ ንጉሡም፣ “ሂዱና የሆነውን ነገር እዩ” ብሎ ከሶርያውያን ሰራዊት በኋላ እንዲሄዱ ላካቸው። 15እነርሱም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ተከተሏቸው። ሶርያውያን በጥድፊያ ሲሸሹ፣ የጣሉትንም ልብስና ዕቃ በየመንገዱ ላይ ተበታትኖ አገኙ፤ መልክተኞቹም ተመልሰው ይህንኑ ለንጉሡ ነገሩት። 16ከዚያም ሕዝቡ ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው አንድ መስፈሪያ ማለፊያ ዱቄት በአንድ ሰቅል፣ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ተሸጠ።

17በዚህ ጊዜ ንጉሡ እጁን ይደግፈው የነበረውን የጦር አለቃ፣ የቅጥሩ በር ኀላፊ አድርጎት ነበርና በበራፉ መተላለፊያ ላይ ሕዝቡ ሲጋፋ ረጋገጠው፤ ያ የእግዚአብሔር ሰው ንጉሡ ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ አስቀድሞ እንደ ተናገረውም የጦር አለቃው ሞተ። 18እንዲሁም የእግዚአብሔር ሰው ለንጉሡ፣ “ነገ በዚሁ ሰዓት በሰማርያ በር ላይ አንድ መስፈሪያ ዱቄት በአንድ ሰቅል፣ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ይሸጣል” ያለውም ተፈጸመ።

19የጦር አለቃው ለእግዚአብሔር ሰው፣ “እግዚአብሔር የሰማይን መስኮቶች ቢከፍት እንኳ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” ብሎት ስለ ነበር፣ የእግዚአብሔር ሰው፣ “ይህን አንተው ራስህ ታያለህ፤ ከዚህ ግን አንዳች አትበላም” ሲል መልሶለት ነበር። 20በበሩ መተላለፊያ ላይ ሕዝቡ ረጋግጦት ስለ ሞተም፣ የተነገረበት በትክክል ደረሰ።

Copyright information for AmhNASV