2 Samuel 10

ዳዊት አሞናውያንን ድል አደረገ

10፥1-19 ተጓ ምብ – 1ዜና 19፥1-19 1ከዚህ በኋላ የአሞናውያን ንጉሥ ሞተ፤ ልጁ ሐኖንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ። 2ዳዊትም፣ “አባቱ ቸርነትን እንዳደረገልኝ ሁሉ፣ እኔም ለናዖስ ልጅ ለሐኖን ወሮታውን ልክፈል” ሲል ዐሰበ። ስለዚህ ስለ አባቱ ሞት የተሰማውን ሐዘን እንዲገልጹለት ዳዊት መልክተኞችን ላከ።

የዳዊት ሰዎች ወደ አሞናውያን ምድር በደረሱ ጊዜ፣
3የአሞናውያን መኳንንት ጌታቸውን ሐኖንን፣ “ዳዊት የተሰማውን ሐዘን ለመግለጽ ሰዎች መላኩ አባትህን ለማክበር አስቦ ይመስልሃል? የላካቸው ሰዎች ከተማዪቱን እንዲመረምሩ፣ እንዲሰልሉና እንዲያጠፏት አይደለምን?” አሉት። 4ስለዚህ ሐኖን የዳዊትን ሰዎች ይዞ፣ የእያንዳንዳቸውን ጢም በከፊል ላጨ፣ ልብሳቸውንም ወገባቸው ድረስ አሳጥሮ በመቍረጥ መልሶ ሰደዳቸው።

5ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ ሰዎቹ እጅግ ዐፍረው ስለ ነበር መልክተኞቹን ላከባቸው፤ ንጉሡም፣ “ጢማችሁ እስኪያድግ በኢያሪኮ ቈዩና ከዚያ በኋላ ተመለሱ” አላቸው።

6አሞናውያን፣ ዳዊት እንደ ጠላቸው ባወቁ ጊዜ፣ ከቤትሮዖብና ከሱባ ሃያ ሺሕ ሶርያውያን እግረኛ ወታደሮችን እንዲሁም ንጉሥ መዓካን ከአንድ ሺሕ ሰዎቹ ጋር ደግሞም ከጦብ ዐሥራ ሁለት ሺሕ ሰዎች ቀጠሩ።

7ዳዊት ይህን ሲሰማ፣ ኢዮአብን ከመላው ተዋጊ ሰራዊት ጋር ላከው። 8አሞናውያን ወጥተው በከተማቸው መግቢያ በር ላይ ተሰለፉ፤ የሱባና የረአብ ሶርያውያን እንዲሁም የጦብና የመዓካ ሰዎች ለብቻ ሜዳው ላይ ተሰለፉ።

9ኢዮአብም ከፊትና ከኋላው ጦር እንደ ከበበው ባየ ጊዜ፣ በእስራኤል ጀግንነታቸው ከታወቀው ጥቂቶቹን መርጦ በሶርያውያን ግንባር አሰለፋቸው። 10የቀሩትን ሰዎች ደግሞ በወንድሙ በአቢሳ ሥር መድቦ በአሞናውያን ግንባር አሰለፋቸው።

11ኢዮአብም እንዲህ አለ፤ ሶርያውያን የሚያይሉብኝ ከሆነ አንተ መጥተህ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን የሚያይሉብህ ከሆነ እኔ መጥቼ እረዳሃለሁ። 12እንግዲህ በርታ፤ ለሕዝባችንና ለአምላካችን ከተሞች በጀግንነት እንዋጋ፤ እግዚአብሔርም በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያድርግ።

13ከዚያም ኢዮአብና አብሮት የነበረው ሰራዊት ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሠ፤ ሶርያውያንም ከፊቱ ሸሹ። 14ሶርያውያን መሸሻቸውን አሞናውያን ባዩ ጊዜ፣ እነርሱም ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ውስጥ ገቡ። ስለዚህም ኢዮአብ አሞናውያንን መውጋቱን አቁሞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

15ሶርያውያን በእስራኤላውያን እንደ ተሸነፉ ባዩ ጊዜ፣ እንደ ገና ተሰባሰቡ። 16አድርአዛር መልክተኞችን ሰድዶ ከወንዙ
የኤፍራጥስ ወንዝ ነው።
ማዶ ያሉትን ሶርያውያን አስመጣ፤ እነርሱም በአድርአዛር ሰራዊት አዛዥ በሶባክ መሪነት ወደ ኤላም ሄዱ።

17ዳዊት ይህን በሰማ ጊዜ፣ መላውን እስራኤልን ሰበሰበ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ ዔላም ሄደ። ሶርያውያንም ለጦርነት ተሰልፈው ዳዊትን በግንባር ገጠሙት፤ 18ይሁን እንጂ ከእስራኤል ፊት ሸሹ፤ ዳዊትም ሰባት መቶ ሠረገለኞችንና አርባ ሺሕ እግረኛ ወታደሮች
የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም እንዲሁም (1ዜና 19፥18 ይመ) ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የዕብራይስጡ፣ ፈረሰኞች ይላል።
ገደለባቸው። እንዲሁም የሰራዊታቸውን አዛዥ ሶባክን አቍስሎት ስለ ነበር፣ እዚያው ሞተ።
19በአድርአዛር ሥር የነበሩት ነገሥታት ሁሉ በእስራኤል መሸነፋቸውን ባዩ ጊዜ ከእስራኤላውያን ጋር ሰላም መሠረቱ፤ ተገዙላቸውም።

ስለዚህም ሶርያውያን ከዚያ በኋላ አሞናውያንን መርዳት ፈሩ።

Copyright information for AmhNASV