2 Samuel 2

ዳዊት የይሁዳ ንጉሥ ሆነ

1ከዚህ በኋላ ዳዊት፣ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ።

እግዚአብሔርም፣ “አዎን ውጣ” አለው።

ዳዊትም፣ “ወደ የትኛዪቱ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ።

እግዚአብሔርም፣ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት።

2ስለዚህ ዳዊት ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ። 3እንዲሁም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ከነቤተ ሰቦቻቸው አመጣቸው፤ እነርሱም በኬብሮን ከተሞች ተቀመጡ። 4የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት።

ሳኦልን የቀበሩት የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፣
5እርሱም የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ይህን እንዲነግሩ መልእክተኞች ላከ፤ “በእንዲህ ዐይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት አሳይታችኋልና እግዚአብሔር ይባርካችሁ፤ 6አሁንም እግዚአብሔር ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ፤ እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፣ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤ 7እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ፤ ጌታችሁ ሳኦል ሞቷልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።”

በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የተደረገ ጦርነት

3፥2-5 ተጓ ምብ – 1ዜና 3፥1-4 8በዚህ ጊዜ የሳኦል ሰራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር፣ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ መሃናይም አሻገረው፤ 9እርሱንም በገለዓድ፣ በአሴር፣ በኢይዝራኤል፣ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ ላይ አነገሠው።

10የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ። 11ዳዊት በኬብሮን ንጉሥ ሆኖ እስራኤልን የገዛው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ።

12የኔር ልጅ አበኔር፣ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ከመሃናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ። 13እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች ወጥተው በገባዖን ኵሬ አጠገብ ተገናኟቸው፤ አንዱ ወገን በኵሬው ወዲህ ማዶ፣ ሌላው ወገን ደግሞ በኵሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ።

14ከዚያም አበኔር፣ ኢዮአብን፣ “ከእናንተም ከእኛም ጕልማሶች ይነሡና በፊታችን በጨበጣ ውጊያ ይጋጠሙ” አለው።

ኢዮአብም፣ “ይሁን እሺ ይጋጠሙ” ብሎ መለሰ።

15ስለዚህ ከብንያም ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፣ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት ሰዎች ተነሥተው ተቈጠሩ። 16ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ በመያዝ ሰይፉን በጐኑ እየሻጠበት ተያይዘው ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ቦታ “የሰይፍ ምድር”
ዕብራይስጡ፤ ሔልቃዝ ሀዙሪም ይባላል፤ ትርጕሙም፣ የመሻሻጥ ምድር ወይም የጥላቻ ምድር ማለት ነው።
ተባለ።

17የዚያን ዕለቱ ጦርነት እጅግ ከባድ ነበር፤ አበኔርና የእስራኤል ሰዎች በዳዊት ሰዎች ድል ሆኑ።

18ሦስቱ የጽሩያ ወንዶች ልጆች ኢዮአብ፣ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤ 19ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል አበኔርን ተከታተለው። 20አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፣ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል ጠየቀው።

እርሱም፣ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት።

21ከዚያም አበኔር፣ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጕልማሳ ይዘህ መሣሪያውን ንጠቀው” አለው። አሣሄል ግን እርሱን መከታተሉን አልተወም ነበር።

22እንደ ገናም አበኔር፣ “እኔን መከታተል ብትተው ይሻልሃል፤ እኔስ ለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት ቀና ብዬ እንዴት አያለሁ?” አለው።

23አሣሄል ግን መከታተሉን አልተወም፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፣ ጦሩም በጀርባው ዘልቆ ወጣ፤ አሣሄልም እዚያው ወደቀ፤ ወዲያው ሞተ። እያንዳንዱም አሣሄል ወድቆ ወደ ሞተበት ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር።

24ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን ተከታተሉት፤ እያሳደዱም ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጋይ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኰረብታ ሲደርሱ ፀሓይ ጠለቀች። 25ከዚያም የብንያም ሰዎች ወደ አበኔር ተሰብስበው ግንባር በመፍጠር በኰረብታው ጫፍ ላይ ተሰለፉ።

26አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፣ “ይህ ሰይፍ ዘላለም ማጥፋት አለበትን? ውጤቱ መራራ መሆኑን አንተስ ሳታውቀው ቀርተህ ነውን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን እንዲያቆሙ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ድረስ ነው?” አለው።

27ኢዮአብም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ባትናገር ኖሮ፣ ሰዎቹ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባላቆሙም ነበር”
ወይም፣ በዚህ ማለዳ ይህን ብትናገር ኖሮ ሰዎቹ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባቆሙ ነበር ወይም፣ ይህን ብትናገር ኖሮ ሰዎቹ እስኪነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባቆሙ ነበር
ብሎ መለሰ።

28ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ በሙሉ እስራኤልን ማሳደዱን ተው፤ ውጊያውም በዚሁ አበቃ።

29አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ዓረባን ዐልፈው ሄዱ፤ ከዚያም ዮርዳኖስን በመሻገር ቢትሮንን
ወይም ማለዳ ወይም ሸለቆ የዕብራይስጡ ቃል ትርጕም በትክክል አይታወቅም።
ሁሉ ዐልፈው ወደ መሃናይም መጡ።

30ከዚያም ኢዮአብ አበኔርን ማሳደዱን ትቶ ተመለሰ፤ ሰዎቹንም ሁሉ አንድ ላይ በሰበሰባቸው ጊዜ፣ ከዳዊት ሰዎች አሣሄልን ሳይጨምር፣ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጥፋታቸው ታወቀ። 31የዳዊት ሰዎች ግን ከአበኔር ጋር ከነበሩት ሦስት መቶ ስድሳ ብንያማውያን ገደሉ። 32አሣሄልንም ከወደቀበት አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት። ከዚያም ኢዮአብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሡ ዐድረው፣ ሲነጋ ኬብሮን ደረሱ።

Copyright information for AmhNASV