Deuteronomy 30

ወደ እግዚአብሔር በመመለስ የሚገኝ በረከት

1በፊትህ ያስቀመጥሁት ይህ በረከትና መርገም ሁሉ በአንተ ላይ ሲመጣና አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በትኖህ በምትኖርበት አሕዛብ መካከል ሆነህ ወደ ልብህ ተመልሰህ ነገሮቹን በምታስተውልበት ጊዜ፣ 2እንዲሁም ዛሬ እኔ በማዝዝህ ሁሉ መሠረት አንተና ልጆችህ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ተመልሳችሁ በፍጹም ልባችሁና በፍጹም ነፍሳችሁ እርሱን ስትታዘዙ፣ 3አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ምርኮህን ይመልስልሃል
ወይም፣ ከግዞት ይመልስሃል
፤ ይራራልሃልም፤ አንተን ከበተነበት አሕዛብ መካከልም እንደ ገና ይሰበስብሃል።
4ከሰማይ በታች እጅግ ሩቅ ወደ ሆነ ምድር ብትጋዝ እንኳ፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ከዚያ ይሰበስብሃል፤ መልሶም ያመጣሃል። 5የአባቶችህ ወደ ሆነችው ምድር ያመጣሃል፤ አንተም ትወርሳታለህ። ከአባቶችህ ይበልጥ ያበለጽግሃል፤ ያበዛሃልም። 6አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ እንድትወድደው፣ በሕይወትም እንድትኖር፣ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የአንተንና የዘርህን ልብ ይገርዛል። 7አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይህን ርግማን ሁሉ በሚጠሉህና በሚያሳድዱህ ጠላቶችህ ላይ ያደርገዋል። 8አንተም ተመልሰህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ትታዘዛለህ፤ ዛሬ እኔ የማዝዝህን ትእዛዝ ሁሉ ትጠብቃለህ። 9ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእጅህ ሥራ ሁሉና በወገብህ ፍሬ፣ በእንስሳትህ ግልገሎችና በምድርህ ሰብል እጅግ ያበለጽግሃል። በአባቶችህ ደስ እንደ ተሰኘ ሁሉ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋልና። 10ይህም የሚሆነው፣ አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ከታዘዝህና በዚህ የሕግ መጽሐፍ የተጻፉትን ትእዛዙንና ሥርዐቱን በመጠበቅ፣ በፍጹም ልብህና በፍጹም ነፍስህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ስትመለስ ነው።

ሕይወትን ወይም ሞትን ስለ መምረጥ

11በዛሬው ዕለት የምሰጥህ ትእዛዝ ይህን ያህል አስቸጋሪ ወይም ከአንተ የራቀች አይደለችም። 12“እንድንፈጽማት አምጥቶ ይነግረን ዘንድ፣ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?” እንዳትል፣ በላይ በሰማይ አይደለችም። 13ደግሞም፣ “እንድናደርጋት አምጥቶ ይነግረን ዘንድ፣ ማን ባሕሩን ይሻገራል?” እንዳትልም፣ ከባሕር ማዶ አይደለችም። 14ነገር ግን ቃሉ ለአንተ በጣም ቅርብ ነው፤ ታደርገውም ዘንድ በአፍህና በልብህ ውስጥ ነው።

15እነሆ፤ ዛሬ ሕይወትንና በረከትን፣ ሞትንና ጥፋትን በፊትህ አኑሬአለሁ። 16አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትወድ፣ በመንገዱም እንድትሄድና ትእዛዙን፣ ሥርዐቱንና ሕጉን እንድትጠብቅ አዝዝሃለሁ፤ ከዚያም በሕይወት ትኖራለህ፤ ትበዛለህም፤ አምላክህም እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትወርሳት ዘንድ በምትገባበት ምድር ይባርክሃል።

17ዳሩ ግን ልብህ ወደ ኋላ ቢመለስና ባትታዘዝ፣ ለሌሎች አማልክት ለመስገድ ብትታለልና ብታመልካቸው፣ 18በርግጥ እንደምትጠፉ እኔ በዛሬው ዕለት እነግራችኋለሁ፤ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ትወርሳት ዘንድ በምትገባባት ምድር ብዙ አትኖሩባትም።

19ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና ርግማንን በፊትህ እንዳስቀመጥሁ ዛሬ ሰማይንና ምድርን ምስክር አድርጌ እጠራብሃለሁ። እንግዲህ አንተና ልጆችህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ፤ 20ይኸውም አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) እንድትወድ፣ ቃሉን እንድታደምጥና ከእርሱ ጋር እንድትጣበቅ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሕይወትህ ነው፤ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ ሊሰጣቸው በማለላቸው ምድር ረዥም ዕድሜ ይሰጥሃል።

Copyright information for AmhNASV