Deuteronomy 9

የሕዝቡ አለመታዘዝ

1እስራኤል ሆይ፤ ስማ፤ ሰማይ ጠቀስ ቅጥር ያላቸው ታላላቅ ከተሞች ያሏቸውን፣ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ አስለቅቀህ ለመግባት ዮርዳኖስን አሁን ትሻገራለህ። 2ዔናቃውያን ብርቱና ቁመተ ረጃጅም ሕዝቦች ናቸው፤ ስለ እነርሱ ታውቃለህ፤ “ዔናቃውያንን ማን ሊቋቋማቸው ይችላል?” ሲባልም ሰምተሃል። 3ይሁን እንጂ እንደሚባላ እሳት ከፊትህ ቀድሞ የሚሻገረው አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) መሆኑን ዛሬ ርግጠኛ ሁን፤ እነርሱን ያጠፋቸዋል፤ በፊትህም ድል ያደርጋቸዋል፤ አንተም እግዚአብሔር (ያህዌ) በሰጠህ ተስፋ መሠረት ታስወጣቸዋለህ፤ በፍጥነትም ትደመስሳቸዋለህ። 4አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነርሱን ከፊትህ ካስወጣቸው በኋላ፣ “ይህችን ምድር እንድወርስ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደዚህ ያመጣኝ፣ ከጽድቄ የተነሣ ነው” ብለህ በልብህ አታስብ። በዚህ አይደለም፤ እነዚህን አሕዛብ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከፊትህ የሚያሳድዳቸው በክፋታቸው ምክንያት ነው። 5ምድራቸውን ገብተህ የምትወርሳት ከጽድቅህ ወይም ከልብህ ቅንነት የተነሣ ሳይሆን፣ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ የማለላቸውን ቃል ለመፈጸም አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) እነዚህን አሕዛብ ከክፋታቸው የተነሣ ከፊትህ ስለሚያባርራቸው ነው። 6ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ይህችን መልካም ምድር እንድትወርሳት የሚሰጥህ ከጽድቅህ የተነሣ አለመሆኑን አስተውል፤ አንተ ዐንገተ ደንዳና ነህና።

የወርቁ ጥጃ

7አምላክህን እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) በምድረ በዳ እንዴት እንዳስቈጣኸው አስታውስ፤ ከቶም አትርሳ። ከግብፅ ከወጣህበት ዕለት አንሥቶ እዚህ ቦታ እስከ ደረስህበት ጊዜ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ እንዳመፅህ ነህ። 8በኮሬብ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለቍጣ አነሣሣችሁት፤ እርሱም እናንተን ሊያጠፋችሁ እጅግ ተቈጣ። 9እኔም የድንጋይ ጽላቶቹን፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ከእናንተ ጋር የገባውን የኪዳን ጽላቶች ለመቀበል ወደ ተራራው በወጣሁ ጊዜ፣ እህል ሳልበላ፣ ውሃም ሳልጠጣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ 10በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰጠኝ፤ በተሰበሰባችሁበት ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ከተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የነገራችሁ ትእዛዞች ሁሉ በእነርሱ ላይ ነበሩባቸው።

11አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከተፈጸመ በኋላ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች ማለትም የኪዳኑን ጽላቶች ሰጠኝ። 12ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “ተነሣ፤ ከግብፅ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ረክሰዋልና ፈጥነህ ከዚህ ውረድ፤ እኔ ካዘዝኋቸው ፈጥነው ፈቀቅ ብለዋል፤ ቀልጦ የተሠራ ጣዖትም ለራሳቸው አበጅተዋል” ብሎ ነገረኝ።

13ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ሕዝብ አይቼዋለሁ፤ በርግጥ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው፣ 14አጠፋቸውና ስማቸውንም ከሰማይ በታች እደመስሰው ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ብዙ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”

15ስለዚህ ተራራው በእሳት እየተቀጣጠለ ሳለ፣ ሁለቱን የቃል ኪዳን ጽላቶች በሁለቱም እጆቼ እንደ ያዝሁ
ወይም፣ ሁለቱም የቃል ኪዳን ጽላቶች ከእኔ ጋር ነበሩ፤ አንዱም በአንዱ፣ ሌላውም በሌላው እጄ ነበር ተብሎ መተርጐም ይችላል።
ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ።
16በርግጥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ላይ ኀጢአት ሠርታችሁ እንደ ነበር ተመለከትሁ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስልም ለራሳችሁ አበጃችሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን ካዘዛችሁ መንገድ በፍጥነት ወጥታችሁ ነበር። 17ስለዚህ ሁለቱን ጽላቶች ወስጄ ከእጆቼ አሽቀንጥሬ በፊታችሁ ሰባበርኋቸው።

18ከዚያም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ክፉ ነገርን በመፈጸም ለቍጣ እንዲነሣሣ የሚያደርገውን ኀጢአት ሁሉ ስለ ሠራችሁ፣ እህል ውሃ ሳልቀምስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንደ ገና በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በግምባሬ ተደፋሁ። 19እናንተን ሊያጠፋችሁ ክፉኛ ተቈጥቶ ነበርና፣ እኔም የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቍጣና መዓት ፈራሁ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ግን እንደ ገና ሰማኝ። 20እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን ሊያጠፋው ክፉኛ ተቈጥቶ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ለአሮንም ጸለይሁ። 21ደግሞም ያን የኀጢአት ሥራችሁን፣ አበጅታችሁት የነበረውን ጥጃ ወስጄ በእሳት አቃጠልሁት፤ ከዚያም ሰባብሬ እንደ ትቢያ ዱቄት እስኪሆን ድረስ ፈጭቼ ከተራራው በሚወርደው ጅረት ውስጥ በተንሁት።

22በተቤራም፣ በማሳህና በቂብሮት ሐታአዋ እግዚአብሔርን (ያህዌ) አስቈጣችሁት።

23 እግዚአብሔር (ያህዌ) ከቃዴስ በርኔ ባስወጣችሁ ጊዜ፣ “ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ርስት አድርጋችሁ ውረሷት” አላችሁ። እናንተ ግን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፤ እርሱን አልታመናችሁበትም፤ አልታዘዛችሁትምም። 24እኔ እናንተን ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ፣ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ።

25 እግዚአብሔር (ያህዌ) እናንተን እንደሚያጠፋችሁ ተናግሮ ስለ ነበር፣ በእነዚያ አርባ ቀናትና አርባ ሌሊቶች በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፋሁ፤ 26እንዲህም በማለት ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ጸለይሁ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ (አዶናይ ያህዌ) በታላቅ ኀይልህ የተቤዠኸውንና በኀያል ክንድህ ከግብፅ ያወጣኸውን፣ ያንተ ርስት የሆነውን ሕዝብህን አታጥፋ። 27ባሪያዎችህን አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን ዐስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፣ ክፋትና ኀጢአት አትመልከት። 28አለዚያ እኛን ካመጣህበት ምድር ያሉ ሰዎች ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ሊያገባቸው ስላልቻለና ስለ ጠላቸው፣ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው’ ይላሉ። 29ነገር ግን እነርሱ በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።”

Copyright information for AmhNASV