Ecclesiastes 8

1ነገሮችን መግለጽ የሚችል፣
እንደ ጠቢብ ያለ ሰው ማን ነው?
ጥበብ የሰውን ፊት ታበራለች፤
የከበደ ገጽታውንም ትለውጣለች።

ንጉሥን ታዘዝ

2በእግዚአብሔር ፊት መሐላ ስለ ፈጸምህ፣ የንጉሥን ትእዛዝ አክብር እልሃለሁ። 3ከንጉሥ ፊት ተጣድፈህ አትውጣ፤ የወደደውንም ማድረግ ስለሚችል ለጥፋት አትሰለፍ። 4የንጉሥ ቃል የበላይ ስለሆነ እርሱን፣ “ምን ታደርጋለህ?” ማን ሊለው ይችላል?

5እርሱን የሚታዘዝ ሁሉ አይጐዳም፤
ጥበበኛም ልብ ትክክለኛውን ጊዜና ተገቢውን አሠራር ያውቃል።
6የሰው መከራ እጅግ ቢጫነውም፣
ለሁሉም ነገር ትክክለኛ ጊዜና ተገቢ አሠራር አለው።

7ሰው የወደ ፊቱን ስለማያውቅ፣
ሊመጣ ያለውን ማን ሊነግረው ይችላል?
8ሰው ነፋስን መቈጣጠር አይችልም
ወይም መንፈሱን ለማቈየት አይችልም

በዕለተ ሞቱም ላይ ሥልጣን ያለው ማንም የለም፤
በጦርነት ጊዜ ማንም ከግዴታ ነጻ እንደማይሆን፣
ክፋትም የሚለማመዷትን አትለቃቸውም።
9ከፀሓይ በታች የተሠራውን ሁሉ በአእምሮዬ መርምሬ፣ ይህን ሁሉ አየሁ። ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ። 10እንዲሁም ወደ ቅዱሱ ስፍራ ይመጡና ይሄዱ የነበሩት ክፉዎች ተቀብረው አየሁ፤ ይህን ባደረጉበት ከተማም ይመሰገኑ ነበር
አንዳንድ የዕብራይስጥ ቅጆችና ሰብዓ ሊቃናት (አቍዊላ) እንዲሁ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ ቅጆች ግን ተረስተዋል ይላሉ።
፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

11በወንጀል ላይ ባፋጣኝ ፍርድ ካልተሰጠ፣ የሰዎች ልብ ክፉን በማድረግ ዕቅድ ይሞላል። 12ኀጥእ መቶ ወንጀል ሠርቶ ዕድሜው ቢረዝምም፣ እግዚአብሔርን የሚያከብሩ፣ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች መልካም እንደሚሆንላቸው ዐውቃለሁ። 13ነገር ግን ክፉዎች እግዚአብሔርን ስለማይፈሩ መልካም አይሆንላቸውም፤ ዕድሜያቸው እንደ ጥላ አይረዝምም።

14በምድር ላይ የሚከሠት ሌላም ከንቱ ነገር አለ፤ ጻድቃን ለክፉዎች የሚገባውን፣ ክፉ ሰዎችም ለጻድቃን የሚገባውን ይቀበላሉ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ነው አልሁ። 15ለሰው፣ ከፀሓይ በታች ከመብላት፣ ከመጠጣትና ከመደሰት ሌላ የተሻለ ነገር ስለሌለ፣ በሕይወት ደስ መሰኘት መልካም ነው አልሁ፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ከፀሓይ በታች በሰጠው የሕይወት ዘመኑ ሁሉ በሥራው ደስታ ይኖረዋል።

16ጥበብን ለማወቅና ሌት ተቀን እንቅልፍ የማያውቀውን በምድር ያለውን የሰውን ድካም ለመገንዘብ በአእምሮዬ ስመረምር፣ 17እግዚአብሔር ያደረገውን ሁሉ አየሁ። ከፀሓይ በታች የሚደረገውን ማንም ሊያውቅ አይችልም፤ ሰው ለመመርመር ብዙ ቢጥርም፣ ትርጕሙን ማግኘት አይችልም፤ ጠቢብም እንኳ ዐውቀዋለሁ ቢል፣ ፈጽሞ ሊገነዘበው አይችልም።

Copyright information for AmhNASV