Ezekiel 16

ኢየሩሳሌም ታማኝ ስላለመሆኗ የተሰጠ ተራዛሚ ተለዋጭ ዘይቤ

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለኢየሩሳሌም አስጸያፊ ተግባሯን ፊት ለፊት ንገራት፤ 3እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲህ ይላታል፤ ዘርሽና ትውልድሽ ከከነዓን ምድር ነው፤ አባትሽ አሞራዊ፣ እናትሽም ኬጢያዊት ነበሩ። 4በተወለድሽበት ቀን ዕትብትሽ አልተቈረጠም፤ ንጹሕ እንድትሆኚ በውሃ አልታጠብሽም፤ በጨው አልታሸሽም፤ በጨርቅም አልተጠቀለልሽም። 5በርኅራኄ ዐይን ተመልክቶሽ ወይም ዐዝኖልሽ ከእነዚህ አንዱን እንኳ ያደረገልሽ ሰው አልነበረም፤ ይልቁንም በተወለድሽበት ቀን ተንቀሽ ስለ ነበር ሜዳ ላይ ተጣልሽ።

6“ ‘እኔም በዚያ ሳልፍ፣ በደምሽ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስትንፈራገጪ አየሁሽ፤ በደምሽም ውስጥ ተኝተሽ ሳለሽ፣ “በሕይወት ኑሪ!”
ጥቂት የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆች ሰብዐ ሊቀናትና ሱርስቱ እንዲሁ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆች ግን “በሕይወት ኑሪ!” በደምሽ ውስጥ ተኝተሽ ሳለሽ “በሕይወት ኑሪ!” አልሁሽ ይላሉ።
አልሁሽ።
7ሜዳ ላይ እንዳለ ቡቃያ አሳደግሁሽ፤ አንቺም አደግሽ፤ ብርቅ ዕንቍ ሆንሽ
ወይም የበሰልሽ ሆንሽ
። ጡቶችሽ አጐጠጐጡ፤ ጠጕርሽም አደገ፤ ነገር ግን ከእናትሽ ማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ነበርሽ።

8“ ‘ዳግመኛም በአጠገብሽ በማልፍበት ጊዜ ወደ አንቺ ተመለከትሁ፤ ለመፈቀርም እንደ ደረስሽ ባየሁ ጊዜ፣ የመጐናጸፊያዬን ዘርፍ በላይሽ ዘርግቼ ዕርቃንሽን ሸፈንሁ። ማልሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር ቃል ኪዳን ተጋባሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺም የእኔ ሆንሽ።

9“ ‘በውሃ ዐጥቤ
ወይም በውሃ ዐጠብሁሽ
ከደም አጠራሁሽ፤ ዘይትም ቀባሁሽ።
10ወርቀ ዘቦ አለበስሁሽ፤ ምርጥ ቈዳ ጫማም አደረግሁልሽ፤ ያማረ በፍታ አለበስሁሽ ውድ መደረቢያም አጐናጸፍሁሽ። 11በጌጣጌጥ አንቈጠቈጥሁሽ፤ በእጅሽ አንባር፣ በዐንገትሽም ድሪ አጠለቅሁልሽ፤ 12በአፍንጫሽ ቀለበት፣ በጆሮሽ ጕትቻ፣ በራስሽም ላይ ውብ አክሊል አደረግሁልሽ፤ 13በወርቅና በብር አጌጥሽ፤ ልብስሽም ያማረ በፍታ፣ ሐርና ወርቀ ዘቦ ነበር፤ ምግብሽም የላመ ዱቄት፣ ማርና የወይራ ዘይት ነበር። እጅግ ውብ ሆንሽ፤ ንግሥት ለመሆንም በቃሽ። 14እኔ ከሰጠሁሽ ሞገስ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም በመሆኑ ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ገነነ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር

15“ ‘ነገር ግን በውበትሽ ተመካሽ፤ ዝናሽንም ለአመንዝራነት ተጠቀምሽበት፤ ከዐላፊ አግዳሚው ጋር ያለ ገደብ አመነዘርሽ፣ ውበትሽም ለማንም ሆነ።
ከአብዛኛዎቹ የጥንት የዕብራይስጥ ቅጆች ጋር ተመሳሳይ ሲሆን አንድ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጅ ግን (አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት የጥንት ቅጆችን ይመ) ከዐላፊ አግዳሚ… አመነዘርሽ፤ እንዲህ ያለው ነገር መሆን የለበትም ይላል።
16ከልብስሽ አንዳንዱን ወስደሽ የምታመነዝሪበትን መስገጃ ስፍራ አስጌጥሽበት፤ እንዲህ ዐይነት ነገር ከዚህ ቀደም አልታየም፤ ወደ ፊትም አይኖርም። 17ከሰጠሁሽ ወርቄና ብሬ የተሠራውን ምርጥ ጌጣጌጥ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አበጀሽ፤ ከእነርሱም ጋር ዝሙት ፈጸምሽ። 18ወርቀ ዘቦ ልብስሽን ወስደሽ ደረብሽላቸው፤ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አቀረብሽ። 19እንድትበዪ የሰጠሁሽን ምግብ ይኸውም ምርጡን ዱቄት፣ ማሩንና የወይራ ዘይቱን መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን አድርገሽ አቀረብሽላቸው፤ እንዲህ ያለ ነገር ተፈጽሟል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር

20“ ‘ለእኔ የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን እንዲበሏቸው ለምስሎቹ ሠዋሽላቸው፤ አመንዝራነትሽ አንሶ ነውን? 21ልጆቼን ዐርደሽ ለጣዖት መሥዋዕት አድርገሽ አቀረብሻቸው።
ወይም በእሳት ውስጥ አሳለፋችኋቸው
22በእነዚህ አስጸያፊ ተግባሮችሽና አመንዝራነትሽ ሁሉ፣ ከእናትሽ ማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ሆነሽ በደምሽ ውስጥ ስትንፈራገጪ የነበርሽበት የሕፃንነትሽ ወራት ትዝም አላለሽ።

23“ ‘ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከሌላው ክፋትሽ ሁሉ በተጨማሪ፣ 24ለራስሽ ጕብታን አበጀሽ፤ በየአደባባዩም የማምለኪያ ኰረብታ ሠራሽ። 25በየመንገዱ መጠምዘዣ ላይም የመስገጃ ኰረብታ አበጀሽ፤ ገላሽን ለዐላፊ አግዳሚው በማቅረብና አመንዝራነትሽን በማበራከት ውበትሽንም አረከስሽ። 26ዘማውያን ከሆኑ ግብፃውያን ጎረቤቶችሽ ጋር አመነዘርሽ፤ ገደብ በሌለው የዝሙት ተግባርሽም ለቍጣ አነሣሣሽኝ። 27ስለዚህ ክንዴን በአንቺ ላይ አንሥቼ ድርጎሽን ቀነስሁ፤ ከክፉ መንገድሽም የተነሣ በብልግናሽ ለሚያፍሩ ጠላቶችሽ ለፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች አሳልፌ ሰጠሁሽ። 28ገና ስላልረካሽም ከአሦራውያን ጋር ደግሞ አመነዘርሽ፤ ከዚያም በኋላ እንኳ አልረካሽም። 29ርኩሰትሽንም እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ባቢሎን
ወይም ካላዲያ
ድረስ አበዛሽ፤ ያም ሆኖ አልረካሽም።

30“ ‘እንደ ዐይን አውጣ አመንዝራ ይህን ሁሉ መፈጸምሽ ምን ዐይነት ደካማ ልብ ቢኖርሽ ነው! ይላል ጌታ እግዚአብሔር 31በየመንገዱ መጠምዘዣ ላይ ጕብታሽን ባበጀሽና በየአደባባዩም መስገጃ ኰረብታ በሠራሽ ጊዜ እንደ ማንኛውም ዝሙት ዐዳሪ አልነበርሽም፤ ምክንያቱም ዋጋ አላስከፈልሽም።

32“ ‘አንቺ ከገዛ ባሏ ይልቅ ሌሎችን የምታስተናግድ አመንዝራ ነሽ! 33ማንኛዋም አመንዝራ ሴት ዋጋ ይከፈላታል፤ አንቺ ግን ለወዳጆችሽ ሁሉ ስጦታ ታበረክቻለሽ፤ ከየአቅጣጫው መጥተው ከአንቺ ጋር ያመነዝሩ ዘንድ እጅ መንሻ ታቀርቢላቸዋለሽ። 34ስለዚህ ያንቺ ግልሙትና ከሌሎቹ የተለየ ነው፤ ማመንዘር የሚሻ ማንም ሰው፣ አንቺን አሳድዶ ማግባባት አያስፈልገውም። ዋጋ ትከፍያለሽ እንጂ አይከፈልሽም፤ አንቺ የሌሎች ፍጹም ተቃራኒ ነሽ።

35“ ‘አንቺ አመንዝራ ሆይ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ! 36ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሀብትሽን
ወይም ምኞትሽን
ስላፈሰስሽ፣ ከወዳጆችሽ ጋር ያለ ገደብ ስላመነዘርሽና ዕርቃንሽን ስለ ገለጥሽ፣ ስለ አስጸያፊዎቹ ጣዖቶችሽ ሁሉና ለእነርሱም የልጆችሽን ደም ስላቀረብሽ፣
37በዚህ ምክንያት ደስ የተሰኘሽባቸውን ወዳጆችሽን፣ የወደድሻቸውንና የጠላሻቸውን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከየአቅጣጫው ሁሉ በዙሪያሽ እሰበስባቸዋለሁ፤ በፊታቸው ዕርቃንሽን እገልጣለሁ፤ እነርሱም ኀፍረተ ሥጋሽን ሁሉ ያያሉ። 38ለአመንዝራና ለነፍሰ ገዳይ ሴቶች የሚገባውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፤ በመዓቴና በቅናቴ እስከ ደም እበቀልሻለሁ። 39ለወዳጆችሽ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም ጕብታሽንና የማምለኪያ ኰረብታሽን ያፈርሳሉ፤ ልብስሽን ይገፉሻል፤ ምርጥ ጌጣጌጥሽን ይቀሙሻል፤ ዕርቃንሽንና ባዶ እጅሽን ያስቀሩሻል። 40ሕዝብ ያነሣሡብሻል፤ በድንጋይ ይወግሩሻል፤ በሰይፍ ይቈራርጡሻል፤ 41ቤቶችሽን ያቃጥላሉ፤ በብዙ ሴቶችም ፊት ቅጣት ያመጡብሻል። ግልሙትናሽን አስተውሻለሁ፤ ከእንግዲህም ለወዳጆችሽ ዋጋ አትከፍዪም። 42በዚህም በአንቺ ላይ የነበረው ቍጣዬ ይበርዳል፤ የቅናቴ ቍጣም ከአንቺ ይርቃል። እኔም ዝም እላለሁ፤ ከእንግዲህም አልቈጣም።

43“ ‘በእነዚህ ነገሮች አስቈጣሽኝ እንጂ የልጅነትሽን ወራት አላሰብሽም፤ ስለዚህ የሥራሽን እከፍልሻለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በሌላው አስጸያፊ ተግባርሽ ሁሉ ላይ ዘማዊነትን አልጨመርሽምን?

44“ ‘በምሳሌ የሚናገር ሁሉ፣ “ሴት ልጅ በእናቷ ትወጣለች” እያለ ይመስልብሻል። 45አንቺ ባሏንና ልጆቿን የምትጸየፍ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የሚጸየፉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ። እናታችሁ ኬጢያዊት፣ አባታችሁም አሞራዊ ነበሩ። 46ታላቂቱ እኅትሽ ከአንቺ በስተ ሰሜን ከሴት ልጆቿ ጋር የምትኖረው ሰማርያ ናት፤ ታናሺቱ እኅትሽም ከአንቺ በስተ ደቡብ ከሴት ልጆቿ ጋር የምትኖረው ሰዶም ናት። 47አንቺም በእነርሱ መንገድ መሄድና አስጸያፊ ተግባራቸውን መከተል ብቻ ሳይሆን፣ ከእነርሱ ይልቅ ፈጥነሽ ምግባረ ብልሹ ሆንሽ። 48እኔ ሕያው እግዚአብሔር! በራሴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺና ሴት ልጆችሽ ያደረጋችሁትን እኅትሽ ሰዶምና ልጆቿ እንኳ አላደረጉትም።

49“ ‘እነሆ የእኅትሽ የሰዶም ኀጢአት ይህ ነበር፤ እርሷና ሴት ልጆቿ እብሪተኞች፣ ጥጋበኞችና ደንታ ቢሶች ነበሩ፤ ድኾችንና ችግረኞችንም አይረዱም ነበር። 50ኵራተኞች ነበሩ፤ በፊቴ አስጸያፊ ተግባር መፈጸማቸውን ባየሁ ጊዜም አስወገድኋቸው። 51ሰማርያ አንቺ ያደረግሽውን ኀጢአት ግማሹን እንኳ አልሠራችም። አንቺ ግን ከእነርሱ የባሰ አስጸያፊ ተግባር በመፈጸምሽ፣ በዚህ ሁሉ እኅቶችሽን ጻድቃን አስመሰልሻቸው። 52እኅቶችሽን እንደ ጻድቃን በማስቈጠርሽ፣ ዕፍረትሽን ተከናነቢ፤ ኀጢአትሽ ከኀጢአታቸው የከፋ ስለሆነ፣ እነርሱ ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ሆኑ። እንግዲህ እኅቶችሽን ጻድቃን ስላስመሰልሻቸው፣ አንቺ ተዋረጂ፤ ዕፍረትሽንም ተከናነቢ።

53“ ‘ነገር ግን የሰዶምንና የሴት ልጆቿን፣ እንዲሁም የሰማርያንና የሴት ልጆቿን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የአንቺንም ምርኮ የእነርሱን በምመልስበት ጊዜ እመልሳለሁ። 54ይህም የሚሆነው ለእነርሱ መጽናኛ በመሆንሽ እንድትዋረጂና ባደረግሽው ሁሉ እንድታፍሪ ነው። 55እኅቶችሽ ሰዶምና ሴት ልጆቿ እንዲሁም ሰማርያና ሴት ልጆቿ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ሁኔታ ይመለሳሉ፤ አንቺና ሴት ልጆችሽም ቀድሞ ወደ ነበራችሁበት ሁኔታ ትመለሳላችሁ። 56በታበይሽበት ወቅት የእኅትሽን የሰዶምን ስም ለመጥራት እንኳ ፈቃደኛ አልነበርሽም፤ 57ይህም ኀጢአትሽ ከመገለጡ በፊት ነበር። አሁን ግን በዙሪያሽ ሆነው ለሚንቁሽ ለኤዶም
ከብዙዎቹ የዕብራይስጥና የሱርስት የጥንት ቅጆች ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ ቅጆች፣ ሰብዐ ሊቃናትና ቩልጌት ግን አራም ይላሉ
ሴት ልጆችና ለጎረቤቶቿ ሁሉ፣ እንዲሁም ለፍልስጥኤም ሴት ልጆች መሣለቂያ ሆነሻል።
58ለብልግናሽና ለአስጸያፊ ተግባርሽ የሚገባውን ቅጣት ትሸከሚያለሽ፤ ይላል እግዚአብሔር

59“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ቃል ኪዳኔን በማፍረስ መሐላዬን ንቀሻልና ተገቢውን ቅጣት ከእኔ ዘንድ ትቀበያለሽ። 60ነገር ግን በልጅነትሽ ጊዜ ከአንቺ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ዐስባለሁ፤ ለዘላለምም የሚኖር ቃል ኪዳን ከአንቺ ጋር እመሠርታለሁ። 61ከአንቺ ታላላቅ የሆኑትንና ታናናሽ የሆኑትን እኅቶችሽን ስትቀበዪ፣ አካሄድሽን ታስቢአለሽ፤ ታፍሪአለሽም። ሴት ልጆች እንዲሆኑሽም እነርሱን ለአንቺ እሰጣለሁ፤ ከአንቺ ጋር በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት ግን አይደለም። 62ስለዚህ ከአንቺ ጋር ቃል ኪዳኔን ዐድሳለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂአለሽ። 63ያደረግሽውን ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፣ በደልሽ ትዝ ሲልሽ ታፍሪያለሽ፤ ከውርደትሽም የተነሣ አፍሽን ከቶ አትከፍቺም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

Copyright information for AmhNASV