Ezekiel 25

በአሞን ላይ የተነገረ ትንቢት

1 የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ አሞናውያን አድርገህ፣ ትንቢት ተናገርባቸው፤ 3እንዲህም በላቸው፤ ‘የጌታ፣ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መቅደሴ በረከሰ ጊዜ፣ የእስራኤልም ምድር ባድማ በሆነች ጊዜ፣ የይሁዳም ቤት ተማርኮ በተወሰደ ጊዜ፣ “ዕሠይ” ብላችኋልና፣ 4ለምሥራቅ ሕዝብ ትገዙ ዘንድ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ እነርሱም በመካከላችሁ ይሰፍራሉ፤ ድንኳኖቻቸውንም በዚያ ይተክላሉ፤ ፍሬያችሁን ይበላሉ፤ ወተታችሁንም ይጠጣሉ። 5የራባን ከተማ የግመሎች መሰማሪያ፣ አሞንንም የበጎች መመሰጊያ አደርጋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 6ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ በልባችሁ ክፋት ሁሉ፣ በእስራኤል ውድቀት ላይ በመደሰት በእጃችሁ አጨብጭባችኋልና፤ በመዝለልም ጨፍራችኋልና 7ክንዴን በእናንተ ላይ አነሣለሁ፤ በአሕዛብ እንድትበዘበዙ አደርጋለሁ፤ ከሕዝቦች መካከል አውጥቼ፣ ከአገሮችም ለይቼ አጠፋችኋለሁ፤ እደመስሳችኋለሁም። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”

በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት

8“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሞዓብና ሴይር፣ “እነሆ የይሁዳ ቤት እንደ ሌሎቹ አሕዛብ ሁሉ ሆነ” ብለዋልና፤ 9በምድሪቱ ድንበር ላይ ካሉትና ክብሯ ከሆኑት ከተሞች ከቤት የሺሞት፣ ከበአልሜዎንና ከቂርያታይም ጀምሬ የሞዓብን ዐምባ እገልጣለሁ። 10ሞዓባውያንንም ከአሞናውያን ጋር ይገዙላቸው ዘንድ፣ ለምሥራቅ ሕዝብ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ አሞናውያን በአሕዛብ ዘንድ ከእንግዲህ መታሰቢያ አይኖራቸውም። 11ሞዓብንም እቀጣለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት

12“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ኤዶም የይሁዳን ቤት ተበቅሏልና፤ በዚህም በደለኛ ሆኗልና፤ 13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ክንዴን በኤዶም ላይ አነሣለሁ፤ ሰዎቹንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ፤ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከቴማንም ጀምሮ እስከ ድዳን ድረስ በሰይፍ ይወድቃሉ። 14በሕዝቤ በእስራኤል አማካይነት ኤዶምን እበቀላለሁ፤ እነርሱም እንደ ቍጣዬና እንደ መዓቴ መጠን በኤዶም ሕዝብ ላይ ያደርጋሉ፤ ኤዶማውያንም በቀሌን ያውቃሉ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት

15“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ፍልስጥኤማውያን በቂም ተነሣሥተው በክፉ ልብ ተበቅለዋልና፣ ይሁዳንም በቈየ ጠላትነት ለማጥፋት ፈልገዋልና፤ 16ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ክንዴን በፍልስጥኤማውያን ላይ አነሣለሁ፤ ከሊታውያንንም እቈርጣለሁ፤ በባሕሩ ጠረፍ ላይ የቀሩትንም አጠፋለሁ። 17በታላቅ በቀል እበቀላቸዋለሁ፤ በመዓቴም እቀጣቸዋለሁ፤” በምበቀላቸውም ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

Copyright information for AmhNASV