Ezra 4:8-24

8አገረ ገዥው ሬሁምና ጸሓፊው ሲምሳይ በኢየሩሳሌም ላይ ለንጉሡ ለአርጤክስስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ጻፉ፤

9ደብዳቤው የተጻፈው፣ ከአገረ ገዥው ሬሁም፣ ከጸሓፊው ሲምሳይ በትሪፖሊስ፣ በፋርስ፣ በአርክ፣ በባቢሎን እንዲሁም በሱሳ ማለትም በኤላማውያን ላይ ዳኞችና ገዦች ከሆኑት ከተባባሪዎቻቸው፣ 10ደግሞም ታላቁና ኀያሉ አስናፈር
በአረማይክ ቋንቋ “አሹርባኒጳል” ማለት ነው።
አፍልሶ በሰማርያ ከተማና ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ እንዲሰፍሩ ካደረጋቸው ሌሎች ሕዝቦች ነው።

11የላኩለት ደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤

ለንጉሥ አርጤክስስ፣

በኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ከሚኖሩት አገልጋዮችህ የተላከ፤

12ከአንተ ዘንድ ወደ እኛ የመጡት አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም በመሄድ ዐመፀኛና ርኩስ ከተማ እንደ ገና በመሥራት ላይ ናቸው፤ ቅጥሮቿንም እንደ ገና በመሥራትና መሠረቶቿንም በመጠገን ላይ መሆናቸው በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን።

13ከዚህም በላይ ይህች ከተማ ከተሠራች፣ ቅጥሮቿም እንደ ገና ከተገነቡ፣ ቀረጥና እጅ መንሻ ወይም ግብር እንደማይከፍሉ፣ የቤተ መንግሥቱም ገቢ እንደሚቀንስ በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። 14አሁንም እኛ ስለ ቤተ መንግሥቱ ስለሚገደን፣ የንጉሡም ክብር ሲነካ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ ሆኖ ስላላገኘነው፣ ይህ ነገር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ እንዲሆን ይህን መልእክት ልከናል፤ 15ስለዚህ በአባቶችህ ቤተ መዛግብት ምርመራ ይደረግ፤ በእነዚህ መዛግብት ውስጥ ይህች ከተማ ዐመፀኛ ከተማ እንደ ሆነች፣ ነገሥታትንና አውራጃዎችን የጐዳችና ከጥንት ጀምሮ የዐመፅ ጐሬ ስለ መሆኗ ማስረጃ ታገኛለህ፤ እንግዲህ ከተማዪቱ የተደመሰሰችው በዚህ ምክንያት ነው። 16ይህች ከተማ ተመልሳ የምትሠራና ቅጥሮቿም እንደ ገና የሚገነቡ ከሆነ፣ ከኤፍራጥስ ማዶ ምንም ነገር እንደማይኖርህ፣ ንጉሥ ታውቅ ዘንድ እንወድዳለን።

17ንጉሡም ይህን መልስ ላከ፤

ለአገረ ገዥው ሬሁም፣ ለጸሓፊው ሲምሳይ፣ በሰማርያና በኤፍራጥስ ማዶ ለሚኖሩ ተባባሪዎቻቸው፤

ሰላም ለእናንተ ይሁን፤

18የላካችሁልኝ ደብዳቤ በፊቴ ተተርጕሞ ተነብቧል። 19እኔም ትእዛዝ ሰጥቼ ምርመራ ተደርጓል፤ በምርመራውም መሠረት ይህች ከተማ ከጥንት ጀምሮ በነገሥታት ላይ ስታምፅ የኖረች የዐመፅና የወንጀል መናኸሪያ እንደ ሆነች ማስረጃ ተገኝቷል። 20ኢየሩሳሌም ከኤፍራጥስ ማዶ ያለውን አገር ሁሉ የገዙ፣ ቀረጥ፣ ግብርና እጅ መንሻም ይቀበሉ የነበሩ ኀያላን ነገሥታት ነበሯት። 21አሁንም እኔ ትእዛዝ እስከምሰጥበት ድረስ ይህች ከተማ እንደ ገና እንዳትሠራ ሥራውን ያቆሙ ዘንድ ለእነዚህ ሰዎች ትእዛዝ አስተላልፉ።

22ይህን ነገር ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ፤ በነገሥታቱ ላይ የሚደርሰው ኪሳራ ለምን እየበዛ ይሄዳል?

23የንጉሡ የአርጤክስስ ደብዳቤ ቅጅ በሬሁም፣ በጸሓፊው በሲምሳይና በተባባሪዎቻቸው ፊት እንደ ተነበበ፣ ወዲያውኑ በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት አይሁድ ሄደው ሥራውን እንዲያቆሙ አስገደዷቸው።

24ስለዚህም በኢየሩሳሌም የሚሠራው የእግዚአብሔር ቤት ሥራ እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ዳርዮስ ዘመነ መንግሥት ሁለተኛ ዓመት ድረስ ተቋረጠ።

Ezra 5

ለዳርዮስ የተላከ የተንትናይ ደብዳቤ

1በዚያን ጊዜ ነቢዩ ሐጌና የአዶ ልጅ ነቢዩ ዘካርያስ፣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ አይሁድ ከእነርሱ በላይ በሆነው በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው። 2ከዚያም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራት ተነሡ፤ የሚያግዟቸውም የእግዚአብሔር ነቢያት አብረዋቸው ነበሩ።

3በዚህ ጊዜ በኤፍራጥስ ማዶ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሄደው፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ውቅሩንም ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው። 4ደግሞም፣ “ይህን ሕንጻ የሚገነቡት ሰዎች ስም ማን ይባላል?” በማለት ጠየቋቸው
የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ይመ፤ የአረማይኩ ትርጕም እንዲህ ይላል፣ ይህን ሕንጻ የሚገነቡትን ሰዎች ስም ነገርናቸው
5የአምላካቸው ዐይን ግን በአይሁድ መሪዎች ላይ ነበረ፤ ነገሩ ወደ ዳርዮስ ደርሶ የጽሑፍ መልስ እስኪያገኙ ድረስ አልተከለከሉም።

6በኤፍራጥስ ማዶ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይ፣ ተባባሪዎቻቸውና በኤፍራጥስ ማዶ የነበሩ ሹማምት ለንጉሥ ዳርዮስ የላኩት ደብዳቤ ቅጅ ይህ ነው፤ 7የላኩትም ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፤

ለንጉሥ ዳርዮስ፣

የከበረ ሰላምታ እናቀርባለን።

8የታላቁ አምላክ ቤተ መቅደስ ወደሚገኝበት ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደን እንደ ነበር በንጉሡ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ሕዝቡ ቤተ መቅደሱን በታላላቅ ድንጋዮች እየገነቡና ቅጥሩንም በወፍራም ምሰሶዎች እየሠሩ ነው፤ ሥራው በትጋት በመከናወንና በእነርሱም አመራር በመፋጠን ላይ ይገኛል።

9እኛም መሪዎቹን፣ “ይህን ቤተ መቅደስ እንደ ገና ለመሥራትና ይህንም ውቅር ለመጠገን የፈቀደላችሁ ማን ነው?” ብለን ጠየቅናቸው። 10የመሪዎቻቸውን ስም በጽሑፍ እናሳውቅህ ዘንድ ስማቸውን ደግሞ ጠየቅን።

11የሰጡን መልስ ይህ ነው፤

“እኛ የሰማይና የምድር አምላክ አገልጋዮች ነን፤ አሁንም እንደ ገና የምንሠራው ቤተ መቅደስ፣ ከብዙ ዘመናት በፊት ታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ሠርቶ የጨረሰውን ነው።
12ነገር ግን አባቶቻችን የሰማይን አምላክ አስቈጥተውት ስለ ነበር፣ ለባቢሎኑ ንጉሥ ለከለዳዊው ናቡከደነፆር አሳልፎ ሰጣቸው፤ እርሱም ይህን ቤተ መቅደስ አፈራርሶ ሕዝቡን ወደ ባቢሎን አፈለሰ።

13“ይሁንና ቂሮስ፣ የባቢሎን ንጉሥ በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ይህን የእግዚአብሔር ቤት እንደ ገና እንዲሠሩ ንጉሥ ቂሮስ ትእዛዝ ሰጠ። 14ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አውጥቶ ባቢሎን በሚገኘው ቤተ መቅደስ
ወይም፣ ቤተ መንግሥት
ውስጥ ያኖራቸውን የእግዚአብሔርን ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች ከባቢሎን ቤተ መቅደስ አስመጣ። ከዚያም ንጉሥ ቂሮስ፣ አገረ ገዥ አድርጎ ለሾመውና ሰሳብሳር ተብሎ ለሚጠራው ሰው ሰጠው፤
15ቀጥሎም፣ ‘እነዚህን ዕቃዎች ይዘህ ሂድና በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ አኑራቸው፤ የእግዚአብሔር ቤት ቀድሞ በነበረበት ቦታ እንደ ገና ይሠራ’ አለው።

16“ስለዚህ ይህ ሰሳብሳር መጥቶ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሠረት ጣለ፤ ከዚያን ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እነሆ በመሠራት ላይ ነው፤ ሆኖም ገና አላለቀም።”

17አሁንም ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ቢሆን፣ ይህ የእግዚአብሔር ቤት በኢየሩሳሌም እንዲሠራ ንጉሥ ቂሮስ በርግጥ ትእዛዝ ሰጥቶ እንደ ሆነ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት የተቀመጡት መዛግብት እንዲመረመሩ ያድርግ፤ ከዚያም ንጉሡ ስለዚህ ጕዳይ የወሰነውን ይላክልን።

Ezra 6:1-18

የዳርዮስ ዐዋጅ

1ከዚያም ንጉሥ ዳርዮስ በባቢሎን ግምጃ ቤት የተቀመጡት መዛግብት እንዲመረመሩ ትእዛዝ ሰጠ። 2በሜዶን አውራጃ በሚገኘው በአሕምታ ከተማ አንድ ጥቅልል ብራና ተገኘ፤ በውስጡም እንዲህ የሚል ቃል ተጽፎበት ነበር፤

ማስታወሻ፤

3በንጉሥ ቂሮስ የመጀመሪያው ዓመት በኢየሩሳሌም ስለሚገኘው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ንጉሡ የሰጠው ትእዛዝ ይህ ነው፤ ቤተ መቅደሱ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ ሆኖ እንደ ገና ይሠራ፤ መሠረቱም ይጣል፤ ቁመቱ ስድሳ ክንድ
27 ሜትር ያህል ነው።
፣ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን፤
4በሦስት ዙር ታላላቅ ድንጋዮችና በአንድ ዙር ዕንጨት ይሠራ፤ ወጪውም ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ይከፈል። 5እንዲሁም ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች፣ በኢየሩሳሌም ወዳለው ቦታቸው ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲመለሱ ይሁን፤ በእግዚአብሔርም ቤት ይቀመጡ።

6አሁንም በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የሆንኸው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና እናንተም በዚያ አውራጃ የምትገኙ ተባባሪዎቻቸው ሁሉ ወደዚያ አትድረሱ። 7በዚህም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሥራ ጣልቃ አትግቡ፤ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት የአይሁድ አገረ ገዥና የአይሁድ መሪዎች በቀድሞው ቦታ ላይ መልሰው ይሥሩት።

8በተጨማሪም የአይሁድ መሪዎች ይህን የእግዚአብሔር ቤት እንደ ገና ሲሠሩ፣ እናንተ ምን እንደምታደርጉላቸው ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ ሥራውም እንዳይቋረጥ የእነዚህ ሰዎች ወጪ በሙሉ ከመንግሥት ግምጃ ቤትና ከኤፍራጥስ ማዶ ከሚገኘው ገቢ ላይ ይከፈል። 9ለሰማይ አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆን ዘንድ የሚያስፈልጋቸውን ነገር፣ ማለት ወይፈኖችን፣ አውራ በጎችንና ተባዕት ጠቦቶችን ስጧቸው፤ እንዲሁም ስንዴው፣ ጨዉ፣ የወይን ጠጁና ዘይቱ በኢየሩሳሌም ያሉት ካህናት በሚጠይቋችሁ መሠረት ያለ ማቋረጥ በየቀኑ ይሰጣቸው። 10ይህ የሚሆነው የሰማይ አምላክን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት እንዲያቀርቡ፣ ለንጉሡና ለወንድ ልጆቹም ደኅንነት እንዲጸልዩ ነው።

11ደግሞም ይህን ትእዛዝ የሚለውጥ ማንም ሰው ቢኖር፣ ከቤቱ ምሰሶ ተነቅሎ በምሰሶው ላይ እንዲሰቀል፣ ስለ ወንጀሉም ቤቱ የቈሻሻ መጣያ እንዲሆን አዝዣለሁ። 12ይህን ትእዛዝ ለማፍረስ ወይም በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ለማጥፋት እጁን የሚያነሣ ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ፣ ስሙን በዚያ እንዲኖር ያደረገ አምላክ ያጥፋው።

እኔ ዳርዮስ በትጋት እንዲፈጸም ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ።

የቤተ መቅደሱ ሥራ ፍጻሜና ምረቃ

13ከዚያም ንጉሡ ዳርዮስ ባዘዘው መሠረት በኤፍራጥስ ማዶ አገረ ገዥ የነበረው ተንትናይ፣ ሰተርቡዝናይና ተባባሪዎቻቸው ሥራው በትጋት እንዲፈጸም አደረጉ። 14ስለዚህ የአይሁድ መሪዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተጽናኑ ሥራውን ቀጠሉ፤ የቤተ መቅደሱንም ሥራ በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ እንዲሁም የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፣ ዳርዮስና አርጤክስስ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ሠርተው ጨረሱ። 15ይህም ቤተ መቅደስ ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ በሚጠራው ወር በሦስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።

16ከዚያም የእስራኤል ሕዝብ፣ ካህናቱ፣ ሌዋውያኑና የቀሩትም ምርኮኞች የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ። 17ለዚህ ለእግዚአብሔር ቤት ምረቃም አንድ መቶ ወይፈኖችን፣ ሁለት መቶ አውራ በጎችንና አራት መቶ ተባዕት ጠቦቶችን ሰጡ፤ ለመላው እስራኤል የኀጢአት መሥዋዕትም ዐሥራ ሁለት ተባዕት ፍየሎችን በእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ ልክ አቀረቡ። 18በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም ላለው ለእግዚአብሔር አገልግሎት ካህናቱን በየማዕረጋቸው፣ ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው መደቧቸው።

Copyright information for AmhNASV