Isaiah 15

በሞዓብ ላይ የተነገረ ትንቢት

1ስለ ሞዓብ የተነገረው ንግር ይህ ነው፤

የሞዓብ ዔር ፈራረሰች፤
በአንድ ሌሊትም ተደመሰሰች።
የሞዓብ ቂር ፈራረሰች፣
በአንድ ሌሊት ተደመሰሰች።
2ዲቦን ወደ መቅደሱ ወጣ፤
ሊያለቅስም ወደ ኰረብታው ሄደ፤
ሞዓብ ስለ ናባው፣ ስለ ሜድባም ዋይታ ያሰማል፤
ራስ ሁሉ ተመድምዷል፤
ጢምም ሁሉ ተላጭቷል።
3በየመንገዱም ማቅ ይለብሳሉ፤
በየሰገነቱና በየአደባባዩ
ሁሉም ያለቅሳሉ፤
እንባም ይራጫሉ።
4ሐሴቦንና ኤልያሊ ጮኹ፤
ድምፃቸው እስከ ያሀጽ ድረስ ተሰማ፤
ስለዚህ የሞዓብ ጦረኞች ጮኹ፤
ልባቸውም ራደ።

5ልቤ ስለ ሞዓብ አለቀሰ፤
ስደተኞቿም እስከ ዞዓር፣
እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ሸሹ፤
እንባቸውን እያፈሰሱ
ወደ ሉሒት ወጡ፤
በሖሮናይም መንገድም፣
ስለ ጥፋታቸው ዋይ እያሉ ነጐዱ።
6የኔምሬ ውሆች ደርቀዋል፤
ሣሩ ጠውልጓል፤
ቡቃያውም ጠፍቷል፤
ለምለም ነገር አይታይም።
7ስለዚህ ያገኙትን ሀብት፣
ያከማቹትን ንብረት ከአኻያ ወንዝ ማዶ ተሸክመው ያሻግሩታል።
8ጩኸታቸው እስከ ሞዓብ ዳርቻ ድረስ ያስተጋባል፤
ዋይታቸው እስከ ኤግላይም፣
ሰቈቃቸውም እስከ ብኤርኢሊም ደረሰ።
9የዲሞን
የማሶሪቱ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የሙት ባሕር ጥቅልል፣ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕምና የቩልጌት ቅጅ ግን፣ ዲቦን ይላሉ።
ወንዞች በደም ተሞልተዋል፤
በዲሞን ላይ ግን ከዚያ ነገር የበለጠ አመጣለሁ፤
ከሞዓብ በሚሸሹት፣
በምድሪቱም ላይ በሚቀሩት አንበሳ እሰድዳለሁ።
Copyright information for AmhNASV