Isaiah 62

አዲሱ የጽዮን ስም

1ጽድቋ እንደ ማለዳ ወጋገን እስኪፈነጥቅ፣
ድነቷ እንደሚያንጸባርቅ ፋና እስኪታይ፣
ስለ ጽዮን ዝም አልልም፤
ስለ ኢየሩሳሌምም ጸጥ አልልም።
2መንግሥታት ጽድቅሽን፣
ነገሥታት ክብርሽን ያያሉ፤
የእግዚአብሔር አፍ በሚያወጣልሽ፣
በአዲስ ስም ትጠሪያለሽ።
3 በእግዚአብሔር እጅ የክብር አክሊል፣
በአምላክሽም እጅ የመንግሥት ዘውድ ትሆኛለሽ።
4ከእንግዲህ፣ “የተተወች” ብለው አይጠሩሽም፤
ምድርሽም፣ “የተፈታች” አትባልም፤
ነገር ግን፣ “ደስታዬ በእርሷ” ትባያለሽ፤
ምድርሽም፣ “ባለ ባል” ትባላለች፤
እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤
ምድርሽም ባለ ባል ትሆናለች።
5ጕልማሳ ድንግሊቱን እንደሚያገባ፣
ልጆችሽ
ወይም፣ ግንበኞችሽ
እንዲሁ ያገቡሻል፤
ሙሽራ በሙሽራዪቱ ደስ እንደሚለው፣
አምላክሽም በአንቺ ደስ ይለዋል።

6ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ዘብ ጠባቂዎችን በቅጥሮችሽ ላይ አቁሜአለሁ፤
ቀንም ሆነ ሌሊት ፈጽሞ አይታክቱም።
እናንት ወደ እግዚአብሔር አቤት፣ አቤት የምትሉ፤
ፈጽሞ አትረፉ፤
7ኢየሩሳሌምን እስኪያጸናት፣
የምድርም ምስጋና እስኪያደርጋት ዕረፍት አትስጡት።

8 እግዚአብሔር በቀኝ እጁ፣
በኀያል ክንዱም እንዲህ ሲል ምሏል፤
“ከእንግዲህ እህልሽን፣
ለጠላቶችሽ መብል እንዲሆን አልሰጥም፤
ከእንግዲህ የደከምሽበትን፣
አዲስ የወይን ጠጅ ባዕዳን አይጠጡትም።
9ነገር ግን መከሩን የሰበሰቡ ይበሉታል፤
እግዚአብሔርንም ያመሰግናሉ፤
የወይኑን ፍሬ የለቀሙም በመቅደሴ
አደባባዮች ይጠጡታል።”

10ዕለፉ፤ በበሮቹ በኩል ዕለፉ፤
ለሕዝቡ መንገድ አዘጋጁ፤
አስተካክሉ፤ ጐዳናውን አስተካክሉ፤
ድንጋዩን አስወግዱ፤
ለመንግሥታትም ምልክት አሳዩ።

11 እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ፣
እንዲህ ሲል ዐውጇል፤
“ለጽዮን ሴት ልጅ፣
‘እነሆ፤ አዳኝሽ መጥቷል፤
ዋጋሽ በእጁ አለ፤
ዕድል ፈንታሽም ከእርሱ ጋር ነው’ በሏት።”
12እነርሱም ቅዱስ ሕዝብ፣
እግዚአብሔር የተቤዣቸው ተብለው ይጠራሉ፤
አንቺም የምትፈለግ፣
ከእንግዲህም የማትተው ከተማ ትባያለሽ።
Copyright information for AmhNASV