Jeremiah 10

ባዕድ አምልኮና እውነተኛው አምልኮ

10፥12-16 ተጓ ምብ – ኤር 51፥15-19 1የእስራኤል ቤት ሆይ፤ እግዚአብሔር የሚላችሁን ስሙ። 2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

“የአሕዛብን መንገድ አትከተሉ፤
እነርሱ በሰማይ ምልክቶች ይታወካሉ፣
እናንተ ግን በእነዚህ አትረበሹ።
3የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፤
ዛፍ ከጫካ ይቈርጣሉ፤
ዐናጺም በመሣሪያው ቅርጽ ያበጅለታል።
4በብርና በወርቅ ይለብጡታል፤
እንዳይወድቅም፣
በመዶሻ መትተው በምስማር ያጣብቁታል።
5ጣዖቶቻቸው በዱባ ዕርሻ መካከል እንደ ቆመ ማስፈራርቾ ናቸው፤
የመናገር ችሎታ የላቸውም፤
መራመድም ስለማይችሉ፣
ተሸካሚ ያስፈልጋቸዋል፤
ጕዳት ማድረስም ሆነ፣
መልካምን ነገር ማድረግ ስለማይችሉ፣
አትፍሯቸው።”
6 እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤
አንተ ታላቅ ነህ፤
የስምህም ሥልጣን ታላቅ ነው።
7የሕዝቦች ሁሉ ንጉሥ ሆይ፤
አንተን የማይፈራ ማነው?
ክብር ይገባሃልና።
ከምድር ጠቢባን ሁሉ፣
ከመንግሥቶቻቸውም ሁሉ መካከል፣
እንደ አንተ ያለ የለም።
8ከከንቱ የዕንጨት ጣዖት ትምህርት የሚቀሥሙ ሁሉ፣
ጅሎችና ሞኞች ናቸው።
9የተጠፈጠፈ ብር ከተርሴስ፣
ወርቅም ከአፌዝ ይመጣል።
ባለሙያውና አንጥረኛው የሠሯቸው፣
ብልኀተኞችም ያበጇቸው ሁሉ፣
ሰማያዊና ሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፈዋል።
10 እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፤
እርሱ ሕያው አምላክ፣ ዘላለማዊም ንጉሥ ነው፤
በሚቈጣበት ጊዜ ምድር ትንቀጠቀጣለች፤
መንግሥታትም ቍጣውን ሊቋቋሙ አይችሉም።
11“እናንተም፣ ‘እነዚህ ሰማያትንና ምድርን ያልፈጠሩ አማልክት ከምድር ላይ፣ ከሰማያትም በታች ይጠፋሉ’ ትሏቸዋላችሁ።”
ይህ ጥቅስ የተጻፈው በአራማይክ ቋንቋ ነው


12እግዚአብሔር ግን ምድርን በኀይሉ ፈጠረ፤
ዓለምን በጥበቡ መሠረተ፤
ሰማያትንም በማስተዋሉ ዘረጋ።
13ድምፁን ሲያንጐደጕድ፣ በሰማያት ያሉ ውሆች ይናወጣሉ፤
ጉሙን ከምድር ዳር ወደ ላይ እንዲወጣ ያደርገዋል፤
መብረቅን ከዝናብ ጋር ይልካል፤
ነፋስንም ከግምጃ ቤቱ ያወጣል።

14እያንዳንዳቸው ጅሎችና ዕውቀት የለሾች ናቸው።
ወርቅ አንጥረኛውም ሁሉ በሠራው ጣዖት ዐፍሯል፤
የቀረጻቸው ምስሎቹ የሐሰት ናቸው፤
እስትንፋስም የላቸውም።
15እነርሱ ከንቱ የፌዝ ዕቃዎች ናቸው፤
ፍርድ ሲመጣባቸው ይጠፋሉ።
16የያዕቆብ ዕድል ፈንታ የሆነው ግን እንደነዚህ አይደለም፤
እርሱ የሁሉ ነገር ፈጣሪ ነውና፤
እስራኤልም የርስቱ ነገድ ነው።
ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው።

ሊመጣ ያለው ግዞት

17አንቺ የተከበብሽ፤
ከያለበት ንብረትሽን ሰብስቢ፤
18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤
“በዚህች ምድር የሚኖሩትን፣
አሁን ወደ ውጪ እወነጭፋቸዋለሁ፤
ጕዳቱ እንዲሰማቸው፣
መከራ አመጣባቸዋለሁ፤”

19ስለ ስብራቴ ወዮልኝ፤
ቍስሌም የማይድን ነው፤
ግን ለራሴ እንዲህ አልሁት፤
“ይህ የኔው ሕመም ነው፤ ልሸከመውም ይገባኛል።”
20ድንኳኔ ፈርሷል፤
ገመዶቹም ሁሉ ተበጣጥሰዋል፤
ልጆቼ ጥለውኝ ሄደዋል፤ ከእንግዲህም አይመለሱም፤
ድንኳኔን ለመትከል፣
መጋረጃዬንም ለመዘርጋት ማንም የቀረ የለም።
21እረኞቹ አእምሮ የላቸውም፤
እግዚአብሔርን አይጠይቁም፤
ስለዚህ አልተከናወነላቸውም፤
መንጎቻቸውም ሁሉ ተበታትነዋል።
22መርዶ ስሙ! እነሆ፤ ከሰሜን ምድር፣
ታላቅ ሽብር እየመጣ ነው፤
የይሁዳን ከተሞች ባድማ፣
የቀበሮዎችም መናኸሪያ ያደርጋል።

የኤርምያስ ጸሎት

23 እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣
አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ
እንደማይችል ዐውቃለሁ።
24 እግዚአብሔር ሆይ፤ ቅጣኝ፤ ብቻ በመጠኑ ይሁንልኝ፤
ፈጽሞ እንዳልጠፋ፣
በቍጣህ አትምጣብኝ።
25ያዕቆብን አሟጥጠው ስለ በሉት፣
ፈጽመው ስለ ዋጡት፣
መኖሪያውንም ወና ስላደረጉ፣
በማያውቁህ ሕዝቦች፣
ስምህንም በማይጠሩ ወገኖች ላይ፣
ቍጣህን አፍስስ።
Copyright information for AmhNASV