Job 15

ኤልፋዝ

1ቴማናዊው ኤልፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፤

2“ጠቢብ ሰው በከንቱ ንግግር መልስ ይሰጣልን?
ወይስ በምሥራቅ ነፋስ ሆዱን ይሞላል?
3በማይረባ ቃል፣
ፍሬ ቢስ በሆነም ንግግር ይከራከራልን?
4አንተ ግን እግዚአብሔርን መፍራት ታጣጥላለህ፤
አምልኮተ እግዚአብሔርን ትከለክላለህ።
5ኀጢአትህ አፍህን ታስተምረዋለች፤
የተንኰለኞችንም አነጋገር መርጠህ ትይዛለህ።
6የሚፈርድብህ አንደበትህ እንጂ እኔ አይደለሁም፣
የሚመሰክርብህም እኔ ሳልሆን የገዛ ከንፈርህ ነው።

7“ለመሆኑ ከሰው ሁሉ ቀድመህ የተወለድህ አንተ ነህን?
ወይስ ከኰረብቶች በፊት ተገኝተሃል?
8በእግዚአብሔር የመማክርት ጉባኤ ላይ ነበርህን?
ጥበብስ የተሰጠው ለአንተ ብቻ ነው?
9እኛ የማናውቀው አንተ ግን የምታውቀው ምን ነገር አለ?
እኛስ የሌለን አንተ ያለህ ማስተዋል የቱ ነው?
10በዕድሜ ከአባትህ የሚበልጡ፣
የሸበቱ ሽማግሌዎች ከእኛ ጋር አሉ።
11የእግዚአብሔር ማጽናናት፣
በርጋታ የተነገረህ ቃል አነሰህን?
12ልብህ ለምን ይሸፍታል?
ዐይንህንስ ምን ያጕረጠርጠዋል?
13በእግዚአብሔር ላይ እንድትቈጣ፣
እንደዚህ ያለ ቃል ከአፍህ እንዲወጣ ያደረገህ ምንድን ነው?

14“ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሰው ምንድን ነው?
ጻድቅስ ይሆን ዘንድ፣ ከሴት የተወለደ ምንድን ነው?
15እነሆ፤ እግዚአብሔር በቅዱሳኑ እንኳ አይታመንም፤
ሰማያትም በእርሱ ፊት ንጹሓን አይደሉም።
16ታዲያ፣ ክፋትን እንደ ውሃ የሚጠጣ፣
አስጸያፊና ርኩስ ሰውማ እንዴት ይታመን!

17“አድምጠኝ፤ በግልጽ አስረዳሃለሁ፤
ያየሁትንም እነግርሃለሁ፤
18ጠቢባን ከአባቶቻቸው የተቀበሉትን፤
ሳይሸሽጉ የተናገሩትን አስረዳሃለሁ፤
19ምድሪቱ ለአባቶቻቸው ተሰጠች፤
በመካከላቸውም ባዕድ አልተቀመጠም፤
20ክፉ ሰው ዕድሜውን ሙሉ፣
ጨካኙም በተመደበለት ዘመን ሁሉ ይሠቃያል።
21የሚያስደነግጥ ድምፅ በጆሮው ላይ ይጮኻል፤
በሰላም ጊዜ ቀማኞች አደጋ ያደርሱበታል።
22ከጨለማ ወጥቶ ማምለጥ ይፈራል፤
ለሰይፍም የተመደበ ነው።
23የአሞራ እራት
ወይም ለአሞራ እራት ለመፈለግ
ለመሆን ይቅበዘበዛል፤
የጨለማ ቀን መቅረቡን ያውቃል።
24ጭንቀትና ሐዘን ያስፈራሩታል፤
ለማጥቃት እንደ ተዘጋጀ ንጉሥም ያይሉበታል፤
25እጁን በእግዚአብሔር ላይ አንሥቷልና፤
ሁሉን የሚችለውን አምላክም ደፍሯል፤
26ወፍራምና ጠንካራ ጋሻ አንግቦ፣
ሊቋቋመው ወጥቷል።

27“ፊቱ በስብ ቢሸፈን፣
ሽንጡ በሥጋ ቢደነድንም፣
28መኖሪያው በፈራረሱ ከተሞች፣
የፍርስራሽ ክምር ለመሆን በተቃረቡ፣
ሰው በማይኖርባቸው ወና ቤቶች ውስጥ ይሆናል።
29ከእንግዲህ ባለጠጋ አይሆንም፤ ሀብቱም አይቈይም፤
ይዞታውም በምድር ላይ አይሰፋም።
30ከጨለማ አያመልጥም፤
ቅርንጫፎቹን ነበልባል ያደርቃቸዋል፤
በእግዚአብሔርም እስትንፋስ ይወሰዳል።
31በአጸፋው አንዳች አያገኝምና፤
ከንቱን ነገር በመታመን ራሱን አያታልል።
32ጊዜው ሳይደርስ ይጠወልጋል፤
ቅርንጫፉም አይለመልምም።
33ፍሬው በጮርቃነት እንደ ተለቀመበት የወይን ተክል፣
አበባውም እንደ ረገፈበት የወይራ ዛፍ ይሆናል።
34የዐመፀኞች ጉባኤ ትመክናለች፤
የጉቦ ሱሰኞችም ድንኳን በእሳት ትበላለች።
35መከራን ይፀንሳሉ፤ ክፋትንም ይወልዳሉ፤
በሆዳቸውም ተንኰል ይጠነስሳሉ።”
Copyright information for AmhNASV