Joshua 2

ረዓብና እስራኤላውያን ሰላዮች

1ከዚያም የነዌ ልጅ ኢያሱ፣ “ሄዳችሁ ምድሪቱን፣ በተለይም የኢያሪኮን ከተማ ሰልሉ” ብሎ ከሰጢም ሁለት ሰላዮች በስውር ላከ፤ ሰዎቹም ሄደው ረዓብ ከተባለች ጋለሞታ
ምናልባትም፣ የእንግዳ ማረፊያ ተጠቃሚ
ቤት ገቡ፤ በዚያም ዐደሩ።

2ለኢያሪኮም ንጉሥ፣ “እነሆ፤ ምድሪቱን ሊሰልሉ ጥቂት እስራኤላውያን በሌሊት ወደዚህ መጥተዋል” ተብሎ ተነገረው። 3የኢያሪኮም ንጉሥ፣ “ወደ አንቺ መጥተው ወደ ቤትሽ የገቡት ሰዎች ምድሪቱን በሙሉ ለመሰለል ስለሆነ፣ እንድታስወጪአቸው” የሚል መልእክት ወደ ረዓብ ላከ።

4ሴቲቱ ግን ሁለቱን ሰዎች ተቀብላ ሸሽጋቸው ስለ ነበር እንዲህ አለች፤ “በርግጥ ሰዎቹ ወደ እኔ መጥተዋል፤ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጡ አላውቅም። 5ጨልሞ የቅጥሩ በር ከመዘጋቱ በፊት ወጥተው ሄደዋል፤ በየት በኩል እንደ ሄዱ ግን እኔ አላውቅም፤ ልትደርሱባቸው ትችላላችሁና ፈጥናችሁ ተከታተሏቸው።” 6ነገር ግን ሰዎቹን ጣራ ላይ አውጥታ በረበረበችው የተልባ እግር ውስጥ ደብቃቸው ነበር። 7ሰዎቹም ሰላዮቹን በመከታተል ወደ ዮርዳኖስ መሻገሪያ የሚወስደውን መንገድ ይዘው ሄዱ፤ አሳዳጆቹ ወጥተው እንደ ሄዱም የቅጥሩ በር ተዘጋ።

8ሰላዮቹ ከመተኛታቸው በፊት ሴቲቱ ወደ ጣራው ወጥታ፣ 9እንዲህ አለቻቸው፤ “እግዚአብሔር ይህችን ምድር እንደ ሰጣችሁ፣ እናንተንም መፍራት እንዳደረብን፣ የዚህች አገር ነዋሪዎች ሁሉ ልባቸው በፊታችሁ መቅለጡንም ዐውቃለሁ። 10ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን
ዕብራይስጡ፣ ያም ሱፍ ይላል፤ ይኸውም የደንገል ባሕር ማለት ነው።
በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ፣ እናንተም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ፈጽሞ ያጠፋችኋቸውን
የዕብራይስጡ ቃል አንድን ሰው ወይም ነገር ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለእግዚአብሔር መስጠት ማለት ነው።
ሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት፣ ሴዎንንና ዐግን ምን እንዳደረጋችኋቸው ሰምተናል።
11ይህን በሰማን ጊዜ ልባችን ቀለጠ፤ እናንተን ከመፍራት የተነሣም ያልተሸበረ ሰው አልነበረም፤ እግዚአብሔር አምላካችሁ በላይም በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ ነውና። 12እንግዲህ እኔ በጎነትን እንዳሳየኋችሁ ሁሉ፣ እናንተም በጎነትን ለአባቴ ቤት እንድታሳዩ በእግዚአብሔር ማሉልኝ፤ መተማመኛ የሚሆን ምልክትም ስጡኝ፤ 13የአባቴንና የእናቴን፣ የወንድሞቼንና የእኅቶቼን እንዲሁም የእነርሱ የሆነውን ነፍስ ሁሉ እንድታተርፉልኝ፤ ከሞትም አድኑን።”

14ሰዎቹም፣ “የእናንተን ሞት ለእኛ ያድርገው! እኛ የምናደርገውን ሁሉ ካልተናገራችሁ፣ እግዚአብሔር ምድሪቱን በሚሰጠን ጊዜ፣ በጎነትና ታማኝነት እናሳይሻለን” አሏት።

15መኖሪያ ቤቷ የከተማውን ቅጥር ተጠግቶ የተሠራ ስለ ነበር፣ ሰዎቹን በመስኮት አሾልካ በገመድ አወረደቻቸው። 16እርሷም፣ “የሚከታተሏችሁ ሰዎች እንዳያገኟችሁ ወደ ኰረብታዎቹ ሂዱ፤ እነርሱ እስኪመለሱም ድረስ ሦስት ቀን በዚያ ተሸሸጉ፤ ከዚያ በኋላ መንገዳችሁን ትቀጥላላችሁ” አለቻቸው።

17ሰዎቹም እንዲህ አሏት፤ “ባማልሽን በዚህ መሐላ የምንያዘው፣ 18ወደ ምድሪቱ በገባን ጊዜ፣ ይህን ቀይ ፈትል እኛን ባወረድሽበት መስኮት ላይ አስረሽ ካንጠለጠልሽው፣ እንዲሁም አባትሽንና እናትሽን፣ ወንድሞችሽንና የአባትሽን ቤተ ሰዎች ሁሉ ወደ ቤትሽ ካመጣሻቸው ብቻ ነው። 19ማንም ከቤትሽ ወጥቶ መንገድ ላይ ቢገኝ፣ ደሙ በራሱ ላይ ነው፤ እኛ አንጠየቅበትም፤ ነገር ግን ከአንቺ ጋር እቤት ውስጥ ያለ ማንኛውም ሰው ከተነካ የደሙ ባለ ዕዳ እኛ እንሆናለን። 20እኛ የምናደርገውን ብትናገሪ ግን፣ ካስማልሽን መሐላ ነጻ እንሆናለን።”

21እርሷም፣ “ይሁን፤ ባላችሁት ተስማምቻለሁ” ስትል መለሰች፤ ከዚያም ሰደደቻቸው፤ እነርሱም ሄዱ፤ ቀይ ፈትሉንም በመስኮቷ ላይ አንጠለጠለችው።

22እነርሱም ወጥተው ወደ ኰረብቶቹ ሄዱ፤ የሚከታተሏቸውም ሰዎች በየመንገዱ ሁሉ ላይ ፈልገውና ዐጥተው እስኪመለሱ ድረስ፣ ሦስት ቀን በዚያው ተሸሸጉ። 23ሁለቱም ሰላዮች ተመለሱ፤ ከኰረብቶቹም ወርደው ወንዙን በመሻገር፣ ወደ ነዌ ልጅ ወደ ኢያሱ መጥተው ያጋጠማቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት። 24ለኢያሱም፣ “በርግጥ እግዚአብሔር ምድሪቱን በሙሉ በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶናል፤ በዚያ የሚኖረውም ሕዝብ ሁሉ እኛን ከመፍራቱ የተነሣ ልቡ መቅለጡን አይተናል” አሉት።

Copyright information for AmhNASV