Judges 18

ዳናውያን ሰዎች በላይሽ ሰፈሩ

1በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ የዳን ነገድም በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስተ ድርሻውን ገና ስላልወሰደ፣ የሚሰፍርበትን የራሱን ርስት ይፈልግ ነበር። 2ስለዚህ ዳናውያን ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ አምስት ኀያላን ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ከተሞች ወደዚያ ላኩ፤ እነዚህም ነገዶቻቸውን ሁሉ የሚወክሉ ነበሩ። የላኳቸውም ሰዎች፣ “ሂዱ፤ ምድሪቱን ሰልሉ” አሏቸው።

መልእክተኞቹም ወደ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር ገቡ፤ ወደሚያድሩበትም ወደ ሚካ ቤት መጡ።
3በሚካ ቤት አጠገብ እንደ ደረሱም የወጣቱን ሌዋዊ ድምፅ ዐወቁ፤ ስለዚህ ወደዚያ ጐራ ብለው፣ “ወደዚህ ያመጣህ ማን ነው? እዚህ ምን ትሠራለህ? የመጣኸውስ ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።

4እርሱም፣ “ሚካ ይህን አደረገልኝ፤ ቀጠረኝ፤ ካህኑም ሆንሁ” አላቸው።

5እነርሱም፣ “መንገዳችን መቃናት አለመቃናቱን እንድናውቅ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅልን” አሉት።

6ካህኑም፣ “በሰላም ሂዱ፤ መንገዳችሁን እግዚአብሔር አቃንቶላችኋል” ብሎ መለሰላቸው።

7ስለዚህ አምስቱ ሰዎች ከዚያ ተነሥተው ወደ ላይሽ መጡ፤ ሲዶናውያን ያለ ሥጋት በጸጥታ
በዕብራይስጡ የዚህ ሐረግ ትርጉም በትክክል አይታወቅም።
እንደሚኖሩ ሁሉ፣ በዚያም የሚኖረው ሕዝብ በሰላም እንደሚኖር አዩ። ምድሪቱ አንዳች የሚጐድላት ነገር ባለመኖሩ ሕዝቡ ባለጠጋ ነበር። እንዲሁም ከሲዶናውያን ርቆ የሚኖር ሲሆን፣ ከማንኛውም ሕዝብ ጋር
በዕብራይስጡ ከዚህ ጋር ሲስማማ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ግን ከአራም ስዎች ጋር ይላል።
ግንኙነት አልነበረውም።

8ወደ ጾርዓና ወደ ኤሽታኦል እንደ ተመለሱ ወገኖቻቸው፣ “የሄዳችሁበት ጕዳይ እንዴት ሆነ?” በማለት ጠየቋቸው።

9መልእክተኞቹም እንዲህ አሏቸው፤ “ምድሪቱ እጅግ መልካም መሆኗን አይተናል፤ እንግዲህ ተነሡ! ሄደን እንዋጋቸው፤ ተነሡ እንጂ ዝም ትላላችሁን? ወደዚያው ሄዳችሁ ምድሪቱን ለመያዝ አታመንቱ፤ 10እዚያ ስትደርሱም ያለ ሥጋት የሚኖር ሕዝብ፣ እግዚአብሔር በእጃችሁ የሚሰጣችሁን አንዳች ነገር ያልጐደላትን ሰፊ ምድር ታገኛላችሁ።”

11ከዚያ በኋላም ከዳን ወገን ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ስድስት መቶ ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሡ። 12ወጥተውም በይሁዳ ምድር ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ እንግዲህ ከቂርያትይዓሪም በስተ ምዕራብ ያለው ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር መባሉ ከዚሁ የተነሣ ነው። 13ከዚያም ተጕዘው ወደ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር በመሄድ ወደ ሚካ ቤት መጡ።

14የላይሽን ምድር ሰልለው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ለወንድሞቻቸው፣ “ከእነዚሁ ቤቶች በአንዱ ኤፉድ፣ ተራፊም፣ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት እንዳለ ታውቃላችሁን? እንግዲህ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ዕወቁበት” አሏቸው። 15ስለዚህ ወጣቱ ሌዋዊ ወደሚኖርበት ወደ ሚካ ቤት ጐራ ብለው ሰላምታ አቀረቡለት። 16ለጦርነት ተዘጋጅተው የመጡት ስድስት መቶ የዳን ሰዎች በቅጥሩ በር መግቢያ ላይ ቆመው ነበር። 17ካህኑ ለጦርነት ከተዘጋጁት ስድስት መቶ ሰዎች ጋር በቅጥሩ በር ላይ ቆሞ ሳለ፣ ምድሪቱን ለመሰለል መጥተው የነበሩትን አምስት ሰዎች ወደ ቤቱ ውስጥ በመግባት የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል ወሰዱ።

18እነዚህ ሰዎች ወደ ሚካ ቤት ገብተው የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል በሚወስዱበት ጊዜ ካህኑ፣ “ምን ማድረጋችሁ ነው?” አላቸው።

19እነርሱም፣ “ዝም በል! አንዲት ቃል እንዳትተነፍስ፤ ከእኛ ጋር ሁን፤ አባትም ካህንም ሁነን፤ ለአንተስ የአንድ ቤተ ሰብ ካህን ከመሆን ይልቅ በእስራኤል የአንዱ ነገድና ጐሣ ካህን ሆነህ ማገልገሉ አይሻልህምን?” አሉት። 20ይህም ካህኑን ደስ አሰኘው፤ እርሱም ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና የተቀረጸውን ምስል ይዞ ከሕዝቡ ጋር ሄደ። 21እነርሱም ሕፃናታቸውን፣ የከብቶቻቸውን መንጋና ሀብታቸውን ሁሉ ወደ ፊት በማስቀደም ተመልሰው ሄዱ።

22ከሚካ ቤት ጥቂት ራቅ እንዳሉም፣ የሚካ ጎረቤቶች ለርዳታ ተጠርተው ተሰበሰቡ፤ የዳን ሰዎችንም ተከታትለው ደረሱባቸው። 23ከበሰተ ኋላቸው ሆነው ሲጮኹባቸውም፣ የዳን ሰዎች ወደ ኋላቸው ዞረው ሚካን፣ “ሰዎችህን ለውጊያ አሰባስበህ መምጣትህ ምን ሆንህና ነው?” አሉት።

24እርሱም፣ “እንዴት፣ ‘ምን ሆንህ’ ብላችሁ ትጠይቁኛላችሁ? የሠራኋቸውን አማልክቴንና ካህኔን ወስዳችሁ ሄዳችኋል፤ ምን የቀረኝ ነገር አለ?” አላቸው።

25የዳን ሰዎች፣ “አትሟገተን፤ ያለዚያ የተቈጡ ሰዎች ጕዳት ላይ ይጥሉሃል፤ አንተም ቤተ ሰብህም ሕይወታችሁን ታጣላችሁ” አሉት። 26የዳን ሰዎች ይህን ብለው መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሚካም የማይችላቸው መሆኑን በማየት ተመልሶ ወደ ቤቱ ሄደ።

27ከዚያም ሚካ የሠራውን ጣዖትና ካህኑን ወስደው ወደ ላይሽ በመሄድ፣ በሰላምና ያለ ሥጋት ይኖር የነበረውን ሕዝብ በሰይፍ መቱት፤ ከተማዪቱንም በእሳት አቃጠሏት። 28የሚኖሩት ከሲዶና በጣም ርቀው ስለ ነበርና ከማንም ጋር ግንኙነት ስላልነበራቸው የሚታደጋቸው አንድም አልነበረም፤ ከተማዪቱም የምትገኘው በቤትሮዓብ አጠገብ ነበረ።

የዳንም ሰዎች ከተማዪቱን እንደ ገና ሠርተው መኖሪያቸው አደረጓት።
29ከተማዪቱንም ከእስራኤል በተወለደው በአባታቸው በዳን ስም ዳን ብለው ጠሯት፤ ቀድሞ ግን ስሟ ላይሽ ይባል ነበር። 30እዚያም የዳን ሰዎች ለራሳቸው ጣዖታት አቆሙ፤ የሙሴ ልጅ፣
ጥንታዊው የዕብራውያን ጸሐፍት ትውፊት፣ አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም እንዲሁም የሱርስቱ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማል፤ የማሶሬቱ ቅጅ ግን ምናሴ ይላል።
የጌርሳም ልጅ ዮናታንና የእርሱም ልጆች ምድሪቱ እስከ ተማረከችበት ጊዜ ድረስ ለዳን ነገድ ካህናት ሆኗቸው፤
31ስለዚህም ሚካ የሠራቸውን ጣዖታት፣ የእግዚአብሔር ቤት በሴሎ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ባለማቋረጥ አመለኳቸው።

Copyright information for AmhNASV