Leviticus 7

የበደል መሥዋዕት

1“ ‘እጅግ ቅዱስ የሆነው የበደል መሥዋዕት የአቀራረብ ሥርዐት ይህ ነው፦ 2የሚቃጠል መሥዋዕት በሚታረድበት ስፍራ የበደሉም መሥዋዕት እዚያው ይታረድ፤ ደሙም በመሠዊያው ላይ ዙሪያውን ይረጭ። 3ሥቡን በሙሉ ያቅርብ፤ ይኸውም፦ ላቱን፣ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሥብ፣ 4ሁለቱ ኵላሊቶች፣ በኵላሊቶቹ ላይና በጐድኑ አጠገብ ያለውን ሥብ እንዲሁም ከኵላሊቶቹ ጋር የሚወጣውን የጕበቱን ሽፋን አብሮ ያቅርብ። 5ካህኑም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት የሚቀርብ አድርጎ በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ይህም የበደል መሥዋዕት ነው። 6ከካህን ወገን የሆነ ወንድ ሁሉ ከዚህ መብላት ይችላል፤ ነገር ግን በተቀደሰ ስፍራ ይበላ፤ ይህም እጅግ ቅዱስ ነው።

7“ ‘የኀጢአት መሥዋዕትና የበደል መሥዋዕት አቀራረብ ሥርዐት አንድ ነው፤ መሥዋዕቶቹ የስርየቱን ሥርዐት ለሚያስፈጽመው ካህን ይሰጣሉ። 8ስለ ማንኛውም ሰው የሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበው ካህን ቈዳውን ለራሱ ይውሰድ። 9በማብሰያ ምድጃ የተጋገረ፣ በመቀቀያ ወይም በምጣድ የበሰለ ማንኛውም የእህል ቍርባን ለሚያቀርበው ካህን ይሰጥ። 10ማናቸውም በዘይት የተለወሰ ወይም ደረቅ የእህል ቍርባን ለአሮን ልጆች ሁሉ እኩል ይሰጥ።

የኅብረት መሥዋዕት

11“ ‘አንድ ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የኅብረት መሥዋዕት
በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል፤ እንዲሁም 13-37 ይመ
በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሊከተለው የሚገባው ሥርዐት ይህ ነው፦

12“ ‘መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ለምስጋና መግለጫ ከሆነ፣ ከምስጋና መሥዋዕቱ ጋር ያለ እርሾ የተጋገረና በዘይት የተለወሰ ኅብስት እርሾ ሳይገባበት፣ በሥቡ ተጋግሮ፣ ዘይት የተቀባ ቂጣ በሚገባ ታሽቶ፣ በዘይት የተለወሰም የላመ ዱቄት ኅብስት አብሮ ያቅርብ። 13ለምስጋና ከሚሆነው የኅብረት መሥዋዕት ጋር፣ በእርሾ የተጋገረ ኅብስት ያቅርብ። 14ከእያንዳንዱም ዐይነት አንዳንድ አንሥቶ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የተለየ ቍርባን በማድረግ ያቅርብ፤ ይህም የኅብረት መሥዋዕቱን ደም ለሚረጨው ካህን ይሰጥ። 15ለምስጋና የሚሆነው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ፣ በቀረበበት ዕለት ይበላ እንጂ አንዳች አይደር።

16“ ‘መሥዋዕቱ ስእለት በመፈጸሙ ወይም በበጎ ፈቃድ የሚቀርብ ከሆነ፣ በቀረበበት ዕለት ይበላ፤ የተረፈውም ሁሉ በማግስቱም ይበላ። 17እስከ ሦስት ቀን የቈየ ማንኛውም የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቃጠል። 18ማንኛውም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ በሦስተኛው ቀን ከተበላ ተቀባይነት የለውም፤ ርኩስ በመሆኑ ላቀረበው ሰው ዋጋ አይኖረውም፤ ከዚያም የበላ ሰው የበደል ዕዳ ይሆንበታል።

19“ ‘ርኩስ ከሆነ ነገር ጋር የተነካካ ሥጋ ይቃጠል እንጂ አይበላ። ሌላውን ሥጋ ግን በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ይብላ፤ 20ነገር ግን ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የቀረበውን የትኛውንም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ከሕዝቡ ፈጽሞ ይወገድ። 21ማንኛውም ሰው የሰውን ርኩሰት ወይም ርኩስ እንስሳን ወይም ማንኛውንም ርኩስ ነገር ቢነካና ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከቀረበው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ያ ሰው ፈጽሞ ከሕዝቡ ይወገድ።’ ”

ሥብና ደም መብላት መከልከሉ

22 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 23“ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የበሬ ወይም የላም፣ የበግ ወይም የፍየል ሥብ አትብሉ። 24ሞቶ የተገኘ ወይም አውሬ የገደለው ከብት ሥብ ለሌላ ተግባር ይዋል እንጂ አይበላ። 25ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ከሚቀርብ
ወይም በእሳት ከቀረበው
እንስሳ ሥብ የሚበላ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ ይወገድ።
26በየትኛውም ቦታ ብትኖሩ የማንኛውንም የወፍ ዘር ወይም የእንስሳ ደም አትብሉ። 27ማንኛውም ሰው ደም ቢበላ፣ ያ ሰው ከሕዝቡ ይወገድ።’ ”

የካህኑ ድርሻ

28 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 29“ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ስለ ራሱ መሥዋዕት አድርጎ ከዚሁ ላይ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ያቅርብ። 30በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርበውን መሥዋዕት በራሱ እጅ ያቅርበው፤ ሥቡን ከፍርምባው ጋር ያቅርብ፤ ፍርምባውን መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ይወዝውዘው። 31ካህኑ ሥቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ፍርምባው ግን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ። 32የኅብረት መሥዋዕታችሁን የቀኝ ወርች ለካህኑ የተለየ አድርጋችሁ ስጡት። 33የኅብረት መሥዋዕቱን ደምና ሥብ የሚያቀርበው የአሮን ልጅ ቀኝ ወርቹን የራሱ ድርሻ አድርጎ ይውሰድ። 34ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት ላይ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች ወስጃለሁ፤ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ከእስራኤላውያን የሚያገኙት መደበኛ ድርሻቸው እንዲሆን ሰጥቻቸዋለሁ።’ ”

35ካህናት ሆነው እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲያገለግሉ በቀረቡ ቀን፣ በእሳት ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ከቀረበው መሥዋዕት ላይ ለአሮንና ለልጆቹ የተመደበላቸው ድርሻ ይህ ነው። 36ካህናቱ በተቀቡበት ቀን፣ እስራኤላውያን መደበኛ ድርሻ አድርገው ከትውልድ እስከ ትውልድ ይህን እንዲሰጧቸው እግዚአብሔር (ያህዌ) አዘዘ።

37እንግዲህ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ የኀጢአት መሥዋዕት፣ የበደል መሥዋዕት፣ የክህነት ሹመት መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ሥርዐት ይህ ነው፤ 38ይህም፣ በሲና ምድረ በዳ እስራኤላውያን መሥዋዕታቸውን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲያቀርቡ ባዘዛቸው ቀን በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጠው ሥርዐት ነው።

Copyright information for AmhNASV