Luke 13

የንስሓ ጥሪ

1በዚህ ጊዜ መጥተው፣ ጲላጦስ ደማቸውን ከመሥዋዕታቸው ጋር ስለ ደባለቀው ስለ ገሊላ ሰዎች ያወሩለት ሰዎች በዚያ ነበሩ። 2እርሱም እንዲህ መለሰላቸው፤ “ታዲያ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ሥቃይ የደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኀጢአተኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋል? 3አይደለም፣ እላችኋለሁ፤ ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ። 4ወይም ደግሞ በሰሊሆም ግንብ ተንዶባቸው የሞቱት ዐሥራ ስምንት ሰዎች በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ በደለኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋል? 5አይደለም፣ እላችኋለሁ፤ ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደዚሁ ትጠፋላችሁ።”

6ደግሞም እንዲህ ሲል ይህን ምሳሌ ተናገረ፤ “አንድ ሰው በወይኑ ዕርሻ ቦታ የተተከለች አንዲት የበለስ ተክል ነበረችው፤ እርሱም ፍሬ ሊፈልግባት መጥቶ ምንም አላገኘም። 7የወይን አትክልት ሠራተኛውንም፣ ‘እነሆ፤ ፍሬ ለማግኘት ልፈልግባት ሦስት ዓመት ወደዚህች በለስ መጥቼ ምንም አላገኘሁም፤ ስለዚህ ቍረጣት፤ ለምን ዐፈሩን በከንቱ ታሟጥጣለች?’ አለው።

8 “እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ጌታ ሆይ፤ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፍግ እስከማደርግላት ድረስ ለዘንድሮ ብቻ ተዋት፤ 9ለከርሞ ካፈራች መልካም ነው፤ አለዚያ ትቈርጣታለህ።’ ”

አንዲት ጐባጣ ሴት በሰንበት ቀን ተፈወሰች

10ኢየሱስ በሰንበት ቀን በአንድ ምኵራብ ያስተምር ነበር። 11በዚያም የድካም መንፈስ ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ አካለ ስንኩል ያደረጋት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርሷም ከመጕበጧ የተነሣ ፈጽሞ ቀና ማለት አትችልም ነበር። 12ኢየሱስም ባያት ጊዜ ጠራትና፣ “አንቺ ሴት፤ ከሕመምሽ ነጻ ወጥተሻል” አላት፤ 13እጁንም በላይዋ ጫነ፤ እርሷም ወዲያው ቀጥ ብላ ቆመች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።

14የምኵራቡ አለቃ ግን፣ ኢየሱስ በሰንበት ቀን ስለ ፈወሰ ተቈጥቶ ሕዝቡን፣ “ሥራ ሊሠራባቸው የሚገባ ስድስት ቀኖች አሉ፤ ስለዚህ በእነዚያ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ እንጂ በሰንበት ቀን አይደለም” አላቸው።

15ጌታም መልሶ እንዲህ አለው፤ “እናንት ግብዞች፤ ከእናንተ መካከል አንድ ሰው በሬውን ወይም አህያውን በሰንበት ቀን ከማደሪያው ፈትቶ ውሃ ሊያጠጣ ይወስደው የለምን? 16ታዲያ፣ ይህች ሴት የአብርሃም ልጅ ሆና ሳለች ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ ስትኖር፣ ከዚህ እስራት በሰንበት ቀን መፈታት አይገባትምን?”

17ይህን በተናገረ ጊዜ ተቃዋሚዎቹ ሁሉ ዐፈሩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ግን እርሱ ባደረገው ድንቅ ሥራ ሁሉ ደስ አላቸው።

የሰናፍጭ ቅንጣትና የእርሾ ምሳሌ

13፥18፡19 ተጓ ምብ – ማር 4፥30-32 13፥18-21 ተጓ ምብ – ማቴ 13፥31-33 18ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት ምን ትመስላለች? ከምንስ ጋር ላመሳስላት? 19አንድ ሰው ወስዶ በዕርሻው ውስጥ የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ አድጋ ዛፍ ሆነች፤ የሰማይ ወፎችም በቅርንጫፎቿ ላይ ሰፈሩ።”

20ደግሞም እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር ላመሳስላት? 21አንዲት ሴት ወስዳ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በዛ ካለ
ግሪኩ ሦስት መስፈሪያ (22 ሊትር የሚያህል) ይላል።
ዱቄት ጋር የደባለቀችውን እርሾ ትመስላለች።”

ጠባቧ በር

22ከዚያ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ ሳለ፣ በሚያልፍባቸው ከተሞችና መንደሮች እያስተማረ ያልፍ ነበር። 23አንድ ሰውም ቀርቦ፣ “ጌታ ሆይ፤ የሚድኑት ጥቂት ሰዎች ብቻ ናቸውን?” አለው።

እርሱም እንዲህ አላቸው፤
24“በጠባቧ በር ለመግባት ተጣጣሩ፤ እላችኋለሁ፤ ብዙዎች ለመግባት ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አይሆንላቸውም። 25የቤቱ ባለቤት ተነሥቶ በሩን ከቈለፈ በኋላ በውጭ ቆማችሁ፣ ‘ጌታ ሆይ፤ ክፈትልን’ እያላችሁ በሩን ማንኳኳት ትጀምራላችሁ።

“እርሱ ግን፣ ‘ማን እንደ ሆናችሁና ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም’ ብሎ ይመልስላችኋል።

26 “እናንተም፣ ‘ከአንተ ጋር አብረን በልተናል፤ ጠጥተናል፤ በአደባባያችንም አስተምረሃል’ ትላላችሁ።

27 “እርሱም፣ ‘እላችኋለሁ፤ ማን እንደ ሆናችሁና ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም፤ እናንት ዐመፀኞች ሁሉ ከእኔ ራቁ’ ይላል።

28 “አብርሃምን፣ ይስሐቅንና ያዕቆብን፣ ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስታዩ፣ እናንተ ግን ወደ ውጭ ተጥላችሁ ስትቀሩ፣ በዚያን ጊዜ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። 29ሰዎች ከምሥራቅ፣ ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ መጥተው በእግዚአብሔር መንግሥት በማእድ ይቀመጣሉ። 30እነሆ፤ ከኋለኞች መካከል ፊተኞች የሚሆኑ፣ ከፊተኞች መካከልም ኋለኞች የሚሆኑ አሉ።”

ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም ዐዘነ

13፥34፡35 ተጓ ምብ – ማቴ 23፥37-39 13፥34፡35 ተጓ ምብ – ሉቃ 19፥41 31በዚያን ጊዜ ከፈሪሳውያን አንዳንዶች መጥተው፣ “ሄሮድስ ሊገድልህ ስለሚፈልግ ተነሥተህ ከዚህ ሂድ” አሉት።

32እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ሄዳችሁ ለዚያ ቀበሮ፣ እነሆ፤ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፤ ሕመምተኞችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ከግቤ እደርሳለሁ ብሏል በሉት፤ 33ይሁን እንጂ ነቢይ ከኢየሩሳሌም ውጭ ይሞት ዘንድ አይገባምና ዛሬና ነገ፣ ከነገ ወዲያም ወደዚያው ጕዞዬን እቀጥላለሁ።

34 “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ነቢያትን የምትገድዪ፣ ወደ አንቺ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግሪ! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ፣ ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግሁ፤ እናንተ ግን እንቢ አላችሁ፤ 35እነሆ፤ ቤታችሁ ወና ሆኖ ቀርቷል። እላችኋለሁ፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ አታዩኝም።”

Copyright information for AmhNASV