Nahum 3

ለነነዌ

1ለደም ከተማ ወዮላት!
ሐሰት፣ ዘረፋም ሞልቶባታል፤
ብዝበዛዋ ተግዞ አያልቅም።
2የጅራፍ ድምፅ፣
የመንኰራኵር ኳኳቴ፣
የፈጣን ፈረስ ኰቴ፣
የሠረገሎች ድምፅ ተሰምቷል።
3ፈረሰኛው ይጋልባል፤
ሰይፍ ይንቦገቦጋል፤
ጦር ያብረቀርቃል።
የሞተው ብዙ ነው፤
ሬሳ በሬሳ ሆኗል፤
ስፍር ቍጥር የለውም፤
መተላለፊያ አልተገኘም።
4ይህ ሁሉ የሆነው ቅጥ ባጣች፣
አሳሳችና መተተኛ በሆነች ዘማዊት ምክንያት ነው፤
እርሷም በዝሙቷ አሕዛብን፣
በጥንቈላዋም ሕዝቦችን ባሪያ ያደረገች ናት።

5የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“እኔ በጠላትነት ተነሥቼብሻለሁ፤
ቀሚስሽን እስከ ፊትሽ እገልበዋለሁ፤
ዕርቃንሽን ለአሕዛብ፣
ኀፍረትሽንም ለነገሥታት አሳያለሁ።
6ቈሻሻ እደፋብሻለሁ፤
እንቅሻለሁ፤
ማላገጫም አደርግሻለሁ።
7የሚያዩሽ ሁሉ ከአንቺ እየሸሹ፣
‘ነነዌ ፈራርሳለች፤ ማን ያለቅስላታል?’ ይላሉ፤
የሚያጽናናሽንስ ከወዴት አገኛለሁ?”
8አንቺ በአባይ ወንዝ አጠገብ ካለችው፣
በውሃ ከተከበበችው፣
ከኖእ አሞን
አንዳንዶች ቴብስ ይላሉ።
ትበልጫለሽን?
ወንዙ መከላከያዋ፣
ውሃውም ቅጥሯ ነው።
9ኢትዮጵያና ግብፅ ወሰን የለሽ ኀይሏ ናቸው፤
ፉጥና ሊቢያም ረዳቶቿ ነበሩ።
10ይሁን እንጂ በምርኮ ተወሰደች፤
ተሰድዳም ሄደች።
በየመንገዱ ማእዘን ላይ፣
ሕፃናቷ ተፈጠፈጡ፤
በመሳፍንቷ ላይ ዕጣ ተጣለ፤
ታላላቅ ሰዎቿ ሁሉ በሰንሰለት ታሰሩ።
11አንቺ ደግሞ ትሰክሪአለሽ፤
ትደበቂአለሽ፣
ከጠላትም መሸሸጊያ ትፈልጊአለሽ።
12ምሽጎችሽ ሁሉ ሊበሉ እንደ ደረሱ
የመጀመሪያ በለስ ፍሬ ናቸው፤
በሚወዛወዙበት ጊዜ፣
ፍሬዎቹ በበላተኛው አፍ ውስጥ ይወድቃሉ።
13እነሆ፤ ጭፍሮችሽ፣
ሁሉም ሴቶች ናቸው!
የምድርሽ በሮች፣
ለጠላቶችሽ ወለል ብለው ተከፍተዋል፤
መዝጊያዎቻቸውንም እሳት በልቷቸዋል።

14ለከበባው ውሃ ቅጅ፤
መከላከያሽን አጠናክሪ፤
የሸክላውን ዐፈር ፈልጊ፤
ጭቃውን ርገጪ፤
ጡቡንም ሥሪ።
15በዚያ እሳት ይበላሻል፤
ሰይፍ ይቈርጥሻል፤
እንደ ኵብኵባም ይግጥሻል።
እንደ ኵብኵባ እርቢ፤
እንደ አንበጣም ተባዢ።
16ከሰማይ ከዋክብት እስኪበልጡ ድረስ፣
የነጋዴዎችሽን ቍጥር አበዛሽ፤
ምድሪቱን ግን እንደ አንበጣ ግጠው አሟጠጡ፤
ከዚያም በርረው ሄዱ።
17ጠባቂዎችሽ እንደ አንበጣ፣
መኳንንትሽም በብርድ ቀን
በቅጥር ሥር እንደሚቀመጥ ኵብኵባ ናቸው፤
ፀሓይ ሲወጣ ግን ይበርራሉ፤
የት እንደሚበርሩም አይታወቅም።

18የአሦር ንጉሥ ሆይ፤ እረኞችህ
ገዦች ማለት ነው።
አንቀላፉ፤
መኳንንትህ ዐርፈው ተኙ፤
ሕዝብህ ሰብሳቢ ዐጥተው፣
በተራራ ላይ ተበትነዋል።
19ቍስልህን ሊፈውስ የሚችል የለም፤
ስብራትህም ለሞት የሚያደርስ ነው።
ስለ አንተ የሰማ ሁሉ፣
በውድቀትህ ደስ ብሎት ያጨበጭባል፤
ወሰን የሌለው ጭካኔህ
ያልነካው ማን አለና?
Copyright information for AmhNASV