Nehemiah 8

1ሕዝቡ ሁሉ “ከውሃ በር” ፊት ለፊት በሚገኘው አደባባይ ላይ እንደ አንድ ሰው ተሰበሰቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር ለእስራኤል ያዘዘውን የሙሴ ሕግ መጽሐፍ እንዲያመጣ ለጸሓፊው ለዕዝራ ነገሩት። 2ስለዚህ ካህኑ ዕዝራ በሰባተኛው ወር የመጀመሪያ ቀን ወንዶች፣ ሴቶችና ማስተዋል የሚችሉ ሁሉ በተገኙበት ጉባኤ ፊት የሕጉን መጽሐፍ አመጣ። 3እርሱም “በውሃ በር” ትይዩ ወደሚገኘው አደባባይ ፊቱን አቅንቶ፣ በወንዶች፣ በሴቶችና በሚያስተውሉ ሰዎች ሁሉ ፊት በመቆም፣ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ ድምፁን ከፍ አድርጎ አነበበ፤ ሕዝቡም ሁሉ የሕጉን መጽሐፍ በጥሞና አደመጡ።

4ጸሓፊው ዕዝራ ለዚሁ ተብሎ በተሠራውና ከፍ ብሎ በሚገኘው የዕንጨት መድረክ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአጠገቡም በስተ ቀኙ በኩል መቲትያ፣ ሽማዕ፣ ዓናያ፣ ኦርዮ፣ ኬልቅያስ፣ መዕሤያ፣ በስተ ግራው በኩል ደግሞ ፈዳያ፣ ሚሳኤል፣ መልክያ፣ ሐሱም፣ ሐሽበዳ፣ ዘካርያስና ሜሱላም ቆመው ነበር።

5ዕዝራም መጽሐፉን ከፈተ፤ ከሕዝቡ ከፍ ብሎ ቆሞ ስለ ነበረ፣ ሁሉም ያዩት ነበረ፣ በከፈተውም ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቆሙ። 6ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገነ፤ ሕዝቡም ሁሉ እጆቻቸውን በማንሣት፣ “አሜን! አሜን!” ብለው መለሱ፤ ከዚህ በኋላ በግምባራቸው ወደ መሬት ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ።

7ሌዋውያኑ ኢያሱ፣ ባኒ፣ ሰራብያ፣ ያሚን፣ ዓቁብ፣ ሳባታይ፣ ሆዲያ፣ መዕሤያ፣ ቆሊጣስ፣ ዓዛርያስ፣ ዮዛባት፣ ሐናን፣ ፌልያ ሕዝቡ በዚያው ቆመው እንዳሉ ሕጉን አስረዷቸው።

8ሕዝቡ የሚነበበውን መረዳት እንዲችሉ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ካነበቡላቸው በኋላ ይተረጕሙላቸውና ይተነትኑላቸው ነበር።

9ከዚያም አገረ ገዥው ነህምያ፣ ካህኑና ጸሓፊው ዕዝራ፣ ሕዝቡንም የሚያስተምሩት ሌዋውያን፣ “ይህች ቀን ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር የተቀደሰች ናት፤ አትዘኑ፤ አታልቅሱም” አሏቸው፤ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ የሕጉን ቃል በሚሰሙበት ጊዜ ያለቅሱ ነበር።

10ነህምያም፣ “ሂዱ፤ ጥሩ ምግብ በመብላት፣ ጣፋጩን በመጠጣት ደስ ይበላችሁ፤ ምንም የተዘጋጀ ነገር ለሌላቸውም ካላችሁ ላይ ከፍላችሁ ላኩላቸው። ይህች ቀን ለጌታችን የተቀደሰች ናት፤ የእግዚአብሔር ደስታ ብርታታችሁ ስለሆነ አትዘኑ” አላቸው።

11ሌዋውያኑም፣ “ይህች ቀን የተቀደሰች ስለሆነች ዝም በሉ፤ አትዘኑም” በማለት ሕዝቡን ሁሉ አረጋጉ።

12ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ የተነገራቸውን ቃል ተረድተው ስለ ነበረ፣ ለመብላት፣ ለመጠጣት፣ ከምግባቸው ከፍለው ለመላክና ሐሤትም ለማድረግ ሄዱ።

13ከወሩም በሁለተኛው ቀን የየቤተ ሰቡ ሁሉ ኀላፊዎች፣ የሕጉን ቃል ለመማር ከካህናቱና ከሌዋውያኑ ጋር በጸሓፊው በዕዝራ ዙሪያ ተሰበሰቡ። 14እስራኤላውያን በሰባተኛው ወር በሚውለው በዓል በዳስ ውስጥ እንዲቀመጡ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጠውን ትእዛዝ በሕጉ ውስጥ ተጽፎ አገኙ፤ 15ስለዚህ በየከተሞቻቸውና በኢየሩሳሌም ይህን ቃል እንዲያውጁና እንዲያሠራጩ እንዲህ በማለት አዘዟቸው፤ “ወደ ኰረብቶች ውጡ፤ ከዘይትና ከበረሓ ወይራ፣ ከባርስነት፣ ከዘንባባና ከለምለም ዛፎች ቅርንጫፎችን አምጡ ፤ በተጻፈው መሠረት ዳሶችን ሥሩ።” 16ስለዚህ ሕዝቡ ወጥተው ቅርንጫፎች አመጡ፤ እያንዳንዳቸውም በየቤታቸው ጣራ ሰገነት፣ በየግቢያቸው፣ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ፣ “በውሃ በር” አደባባይና “በኤፍሬም በር” አደባባይ ላይ ዳስ ሠሩ። 17ከምርኮ የተመለሰውም ማኅበር ሁሉ ዳሱን ሠርቶ ተቀመጠ። ከነዌ ልጅ ከኢያሱ ዘመን ጀምሮ እስከዚያን ጊዜ ድረስ እስራኤላውያን እንደዚያ አድርገው በዓሉን አክብረው አያውቁም፤ ደስታቸውም ታላቅ ነበር።

18ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ፣ ዕዝራ በየዕለቱ ከእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ያነብብ ነበር። እነርሱም በዓሉን ሰባት ቀን አከበሩ፤ በስምንተኛውም ቀን በሕጉ መሠረት የተቀደሰ ጉባኤ ተደረገ።

Copyright information for AmhNASV