Psalms 125

እግዚአብሔር የሚታመኑበትን ይጠብቃል

መዝሙረ መዓርግ።

1 በእግዚአብሔር የሚታመኑ፣
ሳትናወጥ ለዘላለም እንደምትኖር እንደ ጽዮን ተራራ ናቸው።
2ተራሮች ኢየሩሳሌምን እንደ ከበቧት፣
ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም፣ እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው።

3ጻድቃን እጃቸውን ለክፋት እንዳያነሡ፣
የክፉዎች በትረ መንግሥት፣
ለጻድቃን በተመደበች ምድር ላይ አያርፍም።

4 እግዚአብሔር ሆይ፤ መልካም ለሆኑ፣
ልባቸውም ለቀና መልካም አድርግ።
5ወደ ጠማማ መንገዳቸው የሚመለሱትን ግን፣
እግዚአብሔር ከክፉ አድራጊዎች ጋር ያስወግዳቸዋል።

በእስራኤል ላይ ሰላም ይውረድ።
Copyright information for AmhNASV