Psalms 21

ምስጋና ስለ ንጉሡ

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ንጉሥ በኀይልህ ደስ ይለዋል፤
በምትሰጠውም ድል እጅግ ሐሤት ያደርጋል።

2የልቡን መሻት ሰጠኸው፤
የከንፈሮቹንም ልመና አልከለከልኸውም። ሴላ
3መልካም በረከት ይዘህ በመንገዱ ላይ ጠብቀኸው፤
የንጹሕ ወርቅ ዘውድም በራሱ ላይ ደፋህለት።
4ሕይወትን ለመነህ፤
ረዥም ዘመናትንም እስከ ዘላለም ሰጠኸው።
5በአቀዳጀኸው ድል ክብሩ ታላቅ ሆነ፤
ክብርንና ሞገስን አጐናጸፍኸው።

6ዘላለማዊ በረከትን ሰጠኸው፤
ከአንተ ዘንድ በሚገኝ ፍሥሓም ደስ አሰኘኸው፤
7ንጉሡ በእግዚአብሔር ተማምኗልና፤
ከልዑልም ጽኑ ፍቅር የተነሣ፣
ከቆመበት አይናወጥም።

8እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታገኛቸዋለች፤
ቀኝ እጅህም የሚጠሉህን ፈልጋ ትይዛለች።
9በምትገለጥበት ጊዜ፣
እሳት እንደሚንቀለቀልበት ምድጃ ታደርጋቸዋለህ፤
እግዚአብሔር በመዓቱ እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል፤
እሳቱም ሙጥጥ አድርጋ ትበላቸዋለች።
10ዘራቸውን ከምድር፣
ዘር ማንዘራቸውንም ከሰው ልጆች መካከል ታጠፋለህ።
11ክፋት ቢያስቡብህ፣
ተንኰል ቢወጥኑብህም አይሳካላቸውም፤
12በመጡበት ትመልሳቸዋለህና፤
ቀስትህንም በፊታቸው ላይ ታነጣጥራለህ።

13 እግዚአብሔር ሆይ፤ በብርታትህ ከፍ ከፍ በል፤
ኀይልህን እናወድሳለን፤ እንዘምራለንም።
Copyright information for AmhNASV