Psalms 36

የኀጥኡ ክፋት፣ የእግዚአብሔር በጎነት

ለመዘምራን አለቃ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር።

1ክፉውን ሰው፣
በደል በልቡ ታናግረዋለች፤
ወይም …ኀጢአት ከኀጥእ ይመነጫል

እግዚአብሔርን መፍራት፣
በፊቱ የለም፤
2በደሉ ግልጽ ወጥቶ እንዳይጠላ፣
ራሱን በራሱ እጅግ ይሸነግላልና።
3ከአንደበቱ የሚወጣው የክፋትና የተንኰል ቃል ነው፤
ማስተዋልንና በጎ ማድረግን ትቷል።
4በመኝታው ላይ ክፋትን ያውጠነጥናል፤
ራሱን በጎ ባልሆነ መንገድ ይመራል፤
ክፋትንም አያርቅም።

5 እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ እስከ ሰማያት ይደርሳል፤
ታማኝነትህም እስከ ጠፈር ይመጥቃል።
6ጽድቅህ እንደ ታላላቅ ተራሮች፣
ፍርድህም እጅግ ጥልቅ ነው፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ሰውንም እንስሳንም ታድናለህ።
7አምላክ ሆይ፤ ምሕረትህ እንዴት ክቡር ነው!
የሰዎች ልጆች ሁሉ፣
በክንፎችህ ጥላ ሥር መጠጊያ ያገኛሉ።
8ከቤትህ ሲሳይ ይመገባሉ፤
ከበረከትህም ወንዝ ይጠጣሉ።
9የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነውና፣
በብርሃንህ ብርሃንን እናያለን።
10ለሚያውቁህ ምሕረትህ፣
ልባቸውም ለቀና ጽድቅህ ዘወትር አይቋረጥባቸው።
11የትዕቢተኛ እግር በላዬ አይምጣ፤
የክፉውም ሰው እጅ አያሳድደኝ።
12ክፉ አድራጊዎች እንዴት እንደ ወደቁና እንደ ተጋደሙ፣
ቍልቍልም እንደ ተወረወሩና መነሣት እንደማይችሉ ተመልከት!
Copyright information for AmhNASV