Psalms 37

የጻድቁና የክፉው ዕጣ ፈንታ

የዳዊት መዝሙር።

1ዐመፀኞችን በማየት አትሸበር፤
በክፉ አድራጊዎችም አትቅና፤
2እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፤
እንደ ለምለም ቅጠልም ይጠወልጋሉ።

3 በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤
በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ።
4 በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤
የልብህንም መሻት ይሰጥሃል።
5መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤
በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤
6ጽድቅህን እንደ ብርሃን፣
ያንተን ፍትሕ እንደ ቀትር ፀሓይ ያበራዋል።
7 በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤
በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤
መንገዱ በተቃናለት፣
ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር።

8ከንዴት ተቈጠብ፤ ቍጣንም ተወው፤
ወደ እኵይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ።
9ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤
እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ።

10ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤
ስፍራውንም ብታሥሥ አታገኘውም።
11ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤
በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።

12ክፉዎች በጻድቃን ላይ ያሤራሉ፤
ጥርሳቸውንም ያፋጩባቸዋል።
13እግዚአብሔር ግን ይሥቅባቸዋል፣
ቀናቸው እንደ ደረሰ ያውቃልና።

14ድኾችንና ችግረኞችን ለመጣል፣
አካሄዳቸው ቀና የሆነውንም ለመግደል፣
ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፤
ቀስታቸውንም ገተሩ።
15ሰይፋቸው የገዛ ልባቸውን ይወጋል፤
ቀስታቸውም ይሰበራል።

16የጻድቅ ጥቂት ሀብት፣
ከክፉዎች ብዙ ጥሪት ይበልጣል።
17የክፉዎች ክንድ ይሰበራልና፣
ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ደግፎ ይይዛቸዋል።

18 እግዚአብሔር የንጹሓንን የሕይወት ዘመን ያውቃል፤
ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል።
19በክፉ ጊዜ ዐንገት አይደፉም፤
በራብ ዘመንም ይጠግባሉ።
20ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤
የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ መስክ ውበት ይሆናሉ፤
ይጠፋሉ፤ እንደ ጢስም ተነው ይጠፋሉ።

21ኀጢአተኛ ይበደራል፤ መልሶም አይከፍልም፤
ጻድቅ ግን ይቸራል።
22 እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤
እርሱ የሚረግማቸው ግን ይጠፋሉ።

23የሰው አካሄድ በእግዚአብሔር ይጸናል፤
በመንገዱ ደስ ይለዋል።
24ቢሰናከልም አይወድቅም፣
እግዚአብሔር በእጁ ደግፎ ይይዘዋልና።

25ጕልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤
ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣
ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም።
26ሁልጊዜ ቸር ነው፤ ያበድራልም፤
ልጆቹም የተባረኩ ይሆናሉ።

27ከክፉ ራቅ፤ መልካሙንም አድርግ፣
ለዘላለምም ትኖራለህ።
28 እግዚአብሔር ፍትሕን ይወድዳልና፣
ታማኞቹንም አይጥልም፤
ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤
የኀጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል።
29ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤
በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ።

30የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤
አንደበቱም ፍትሐዊ ነገር ያወራል።
31የአምላኩ ሕግ በልቡ አለ፤
አካሄዱም አይወላገድም።

32ክፉዎች ጻድቁን ይከታተሉታል፤
ሊገድሉትም ይሻሉ።
33 እግዚአብሔር ግን በእጃቸው አይጥለውም፤
ፍርድ ፊት ሲቀርብም አሳልፎ አይሰጠውም።
34 እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤
መንገዱንም ጠብቅ፤
ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤
ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ።

35ክፉና ጨካኙን ሰው፣
እንደ ሊባኖስ ዝግባ ለምልሞ አየሁት፤
36ዳግመኛ በዚያ ሳልፍ፣ እነሆ፣ በቦታው አልነበረም፤
ብፈልገውም አልተገኘም።

37ንጹሓንን ልብ በል፤ ቅኑንም አስተውል፤
የሰላም ሰው ተስፋ አለውና።
ወይም ዘር ይወጣለታል

38ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይጠፋሉ፤
የክፉዎችም ዘር
ወይም ትውልድ
ይወገዳል።

39የጻድቃን ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤
በመከራ ጊዜም መጠጊያቸው እርሱ ነው።
40 እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፤
ይታደጋቸዋልም፤
ከክፉዎች እጅ ነጥቆ ያወጣቸዋል፤
እርሱን መጠጊያ አድርገዋልና ያድናቸዋል።
Copyright information for AmhNASV