Psalms 70

የጭንቀት ጩኸት

70፥1-5 ተጓ ምብ – መዝ 40፥13-17

ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር፤ ለመታሰቢያ።

1አምላክ ሆይ፤ ታድነኝ ዘንድ ዘንበል በል፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

2ሕይወቴን ለማጥፋት የሚሹ፣
ይፈሩ፤ ሁከትም ይምጣባቸው፤ የእኔን መጐዳት የሚመኙ፣
በውርደት ወደ ኋላቸው ይመለሱ።
3በእኔ ላይ፣ “ዕሠይ! ዕሠይ!” የሚሉ፣
ተሸማቅቀው ወደ ኋላ ይመለሱ።
4ነገር ግን የሚሹህ ሁሉ፣
በአንተ ሐሤት ያድርጉ፤ ደስም ይበላቸው፤
“ማዳንህን የሚወድዱ ሁሉ ሁልጊዜ፣
እግዚአብሔር ከፍ ይበል!” ይበሉ።

5እኔ ግን ምስኪንና ችግረኛ ነኝ፤
አምላክ ሆይ፤ ፈጥነህ ድረስልኝ፤
ረዳቴም፣ ታዳጊዬም አንተ ነህና፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ አትዘግይ።
Copyright information for AmhNASV