Psalms 76

ግርማው ለሚያስፈራው አምላክ የቀረበ ቅኔ

ለመዘምራን አለቃ፤ በበገናዎች፤ የአሳፍ መዝሙር ማሕሌት።

1እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ፤
ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው።
2ድንኳኑ በሳሌም፣
ማደሪያውም በጽዮን ነው።
3በዚያም ተወርዋሪውን ፍላጻ፣
ጋሻንና ሰይፍን፣ ጦርንም ሰበረ። ሴላ

4አንተ ብርሃን ተላብሰህ ደምቀሃል፤
ግርማዊነትህም ከዘላለም ተራሮች ይልቃል።
5ልበ ሙሉ የሆኑት ተዘርፈዋል፤
አንቀላፍተውም ተኝተዋል፤
ከጦረኞቹም መካከል፣
እጁን ማንቀሳቀስ የቻለ የለም።
6የያዕቆብ አምላክ ሆይ፤ ከተግሣጽህ የተነሣ፣
ፈረስና ፈረሰኛው ጭልጥ ብለው ተኝተዋል።

7መፈራት ያለብህ አንተ ብቻ ነህ፤
በተቈጣህ ጊዜ ማን በፊትህ መቆም ይችላል?
8አንተ ፍርድን ከሰማይ አሰማህ፤
ምድርም ፈርታ ጸጥ አለች፤
9አምላክ ሆይ፤ ይህም የሆነው አንተ የምድር ጐስቋሎችን ለማዳን፣
ለፍርድ በተነሣህ ጊዜ ነው። ሴላ
10ሰውን ብትቈጣ እንኳ ለክብርህ ይሆናል፤
ከቍጣ የተረፉትንም ትገታቸዋለህ።
በሕዝብህ ላይ የምታወርደው ቍጣ ለክብርህ ይሆናል ወይም በቍጣውም መታሰቢያነት ራስህን ታስታጥቃለህ የሚሉ አሉ።


11ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ተሳሉ፤ ስእለቱንም አግቡ፤
በእርሱ ዙሪያ ያሉ ሁሉ፣
አስፈሪ ለሆነው ለእርሱ እጅ መንሻ ያምጡ።
12እርሱ የገዦችን መንፈስ ይሰብራል፤
በምድር ነገሥታትም ዘንድ የተፈራ ነው።
Copyright information for AmhNASV