Psalms 99

ጻድቅና ቅዱስ አምላክ

1 እግዚአብሔር ነገሠ፤
ሕዝቦች ይንቀጥቀጡ፤
በኪሩቤል ላይ በዙፋን ተቀምጧል፤
ምድር ትናወጥ።
2 እግዚአብሔር በጽዮን ታላቅ ነው፤
ከሕዝቦችም ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ብሏል።
3ታላቁንና አስፈሪውን ስምህን ይወድሱ፤
እርሱ ቅዱስ ነው።

4ፍትሕን የምትወድድ፣ ኀያል ንጉሥ ሆይ፤
አንተ ትክክለኝነትን መሠረትህ፤
ፍትሕንና ቅንነትንም፣
ለያዕቆብ አደረግህ።
5አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፤
በእግሩ መርገጫ ስገዱ፤
እርሱ ቅዱስ ነውና።

6ሙሴና አሮን ካህናቱ ከሆኑት መካከል ነበሩ፤
ሳሙኤልም ስሙን ከጠሩት መካከል አንዱ ነበረ፤
እነርሱ ወደ እግዚአብሔር ተጣሩ፤
እርሱም መለሰላቸው።
7ከደመና ዐምድ ውስጥ ተናገራቸው፤
እነርሱም ሥርዐቱንና የሰጣቸውን ድንጋጌ ጠበቁ።

8 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤
አንተ መለስህላቸው፤
ጥፋታቸውን
ወይም የተፈጸመባቸውን በደል ማለት ነው።
ብትበቀልም እንኳ፣
አንተ ይቅር የምትላቸው አምላክ ነህ።
9አምላካችንን እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ አድርጉት፤
በቅዱስ ተራራውም ላይ ስገዱ፤
አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና።
Copyright information for AmhNASV