Zechariah 10

እግዚአብሔር ለይሁዳ ይጠነቀቃል

1የበልግ ዝናብ እንዲሰጣችሁ እግዚአብሔርን ጠይቁ፤
ማዕበሉን ደመና የሚያደርግ እግዚአብሔር ነው፤
እርሱ ለሰዎች በቂ ዝናብን፣
ለእያንዳንዱም የምድርን ተክል ይሰጣል።
2ተራፊም አሳሳች ነገር ይናገራል፤
ሟርተኞች የሐሰት ራእይ ያያሉ፤
የውሸት ሕልም ይናገራሉ፤
ከንቱ መጽናናት ይሰጣሉ፤
ስለዚህ ሕዝቡ እንደ በጎች ተቅበዘበዙ፤
እረኛ በማጣትም ተጨነቁ።

3“ቍጣዬ በእረኞች ላይ ነድዷል፤
መሪዎችንም እቀጣለሁ፤
እግዚአብሔር ጸባኦት፣
ለመንጋው ለይሁዳ ቤት ይጠነቀቃልና፤
በጦርነትም ጊዜ እንደ ክብሩ ፈረስ ያደርጋቸዋል።
4ከይሁዳ፣ የማእዘን ድንጋይ፣
የድንኳን ካስማ፣
የጦርነት ቀስት፣
ገዥም ሁሉ ይወጣል።
5ጠላትን መንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ ይረጋግጣሉ፤
በአንድነት
ወይም ሁሉም ገዦች በአንድነት ማለት ነው 5 እነርሱም
እንደ ጦር ሰልፈኛ ይሆናሉ፤
እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለሆነ ተዋግተው፤
ፈረሰኞችን ያዋርዳሉ።

6“የይሁዳን ቤት አበረታለሁ፤
የዮሴፍንም ቤት እታደጋለሁ።
ስለምራራላቸው፣
ወደ ቦታቸው እመልሳቸዋለሁ፤
እነርሱም በእኔ እንዳልተተዉ ሰዎች
ይሆናሉ፤
እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝና፣
ጸሎታቸውን እሰማለሁ።
7ኤፍሬማውያን እንደ ኀያላን ሰዎች ይሆናሉ፤
ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደ ጠጣ ሰው ሐሤት ያደርጋል።
ልጆቻቸው ያዩታል፤ ደስተኛም ይሆናሉ፤
ልባቸውም በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል።
8በፉጨት እጠራቸዋለሁ፤
በአንድነት እሰበስባቸዋለሁ፤
በርግጥ እቤዣቸዋለሁ፤
እንደ ቀድሞው ይበዛሉ።
9በሕዝቦች መካከል ብበትናቸውም፣
በሩቅ ምድር ሆነው ያስቡኛል፤
እነርሱና ልጆቻቸው ተርፈው፣
በሕይወት ይመለሳሉ።
10ከግብፅ እመልሳቸዋለሁ፤
ከአሦርም እሰበስባቸዋለሁ፤
ወደ ገለዓድና ወደ ሊባኖስ አመጣቸዋለሁ፤
በቂ ስፍራም አይገኝላቸውም።
11በመከራ ባሕር ውስጥ ያልፋሉ፤
የባሕሩ ማዕበል ጸጥ ይላል፤
የአባይም ጥልቅ ሁሉ ይደርቃል።
የአሦር ትምክሕት ይዋረዳል፤
የግብፅም በትረ መንግሥት ያበቃል።
12 በእግዚአብሔር አበረታቸዋለሁ፤
በስሙም ይመላለሳሉ”
ይላል እግዚአብሔር
Copyright information for AmhNASV