1 Chronicles 11

ዳዊት በእስራኤል ላይ ነገሠ

11፥1-3 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥1-3

1እስራኤል ሁሉ በኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ እኛ የገዛ ሥጋህና ደምህ ነን፤ 2በቀደመው ዘመን ሳኦል ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን ወደ ጦርነት የምትመራ አንተ ነበርህ፤  እግዚአብሔር አምላክህም፣ ‘ሕዝቤን እስራኤልን የምትጠብቅ አንተ ነህ፤ ንጉሣቸውም ትሆናለህ’ ብሎሃል”።

3የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ ንጉሥ ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጡ፤ ዳዊትም በኬብሮን  በእግዚአብሔር ፊት ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገባ።  እግዚአብሔር በሳሙኤል አማካይነት በሰጠው ተስፋ መሠረት ዳዊትን ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት።

ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል አደረገ

11፥4-9 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 5፥6-10

4ዳዊትና እስራኤላውያን ሁሉ ኢያቡስ ወደምትባለው ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ ኢያቡሳውያን 5ዳዊትን “ወደዚህ ፈጽሞ አትገባም” አሉት፤ ዳዊት ግን የጽዮንን ምሽግ ያዘ፤ እርሷም የዳዊት ከተማ ናት።

6ዳዊትም፣ “ኢያቡሳዊያንን ቀድሞ የሚወጋ ሰው የሰራዊቱ አዛዥ ይሆናል” አለ፤ ስለዚህ የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ በመጀመሪያ ወጣ፤ እርሱም አዛዥ ለመሆን በቃ።

7ከዚያም ዳዊት መኖሪያውን በዐምባዪቱ ውስጥ አደረገ፤ ከዚህም የተነሣ የዳዊት ከተማ ተባለች። 8ዳዊትም ከሚሎ ጀምሮ የከተማዪቱን ዙሪያ ቅጥር ሠራ፤ ኢዮአብ ደግሞ የቀረውን የከተማዪቱን ክፍል መልሶ ሠራ። 9 እግዚአብሔር ጸባኦት ከእርሱ ጋር ስለ ነበር ዳዊት በየጊዜው እየበረታ ሄደ።

የዳዊት ኀያላን ሰዎች

11፥10-41 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 23፥8-39

10የዳዊት ኀያላን ሰዎች አለቆች እነዚህ ናቸው፤ እነርሱም  እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት መንግሥቱ በምድሪቱ ሁሉ ትሰፋ ዘንድ ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋር ሆነው ለመንግሥቱ ብርቱ ድጋፍ ሰጡ። 11የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም ዝርዝር ይህ ነው፤

ሐክሞናዊው ያሾብዓም የጦር መኮንኖቹ አለቃ
ሠላሳ ወይም እንደ አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጒሞች፣ ሦስት (እንዲሁም 2ሳሙ 23፥8 ይመ) ይላሉ
ነበረ፤ እርሱም ጦሩን አንሥቶ በአንድ ጊዜ ሦስት መቶ ሰው ገደለ።

12ከእርሱም ቀጥሎ ከሦስቱ ኀያላን አንዱ የሆነው የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ አልዓዛር ነው፤ 13እርሱም ፍልስጥኤማውያን ለጦርነት በተሰበሰቡ ጊዜ በፈስደሚም ከዳዊት ጋር አብሮ ነበረ፤ ገብስ በሞላበት የእርሻ ቦታ ወታደሮቹ ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ 14ይሁን እንጂ በእርሻው መካከል ቦታ ይዘው ስለ ነበረ ፍልስጥኤማውያንን ገደሉ፤  እግዚአብሔርም ታላቅ ድል ሰጣቸው።

15ከፍልስጥኤማውያን ሰራዊት ጥቂቱ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ሳለ፣ ከሠላሳዎቹ አለቆች ሦስቱ ዳዊትን ለመገናኘት በዓዶላም ዋሻ አጠገብ ወደሚገኘው ወደ ዐለቱ ወረዱ። 16በዚያን ጊዜ ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያን ሰራዊት ደግሞ በቤተልሔም ነበረ። 17ዳዊትም ውሃ ፈልጎ ነበርና፣ “ከቤተ ልሔም በር አቅራቢያ ከሚገኘው ጒድጓድ የምጠጣው ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ። 18በዚህ ጊዜ ሦስቱ የፍልስጥኤማውያንን ሰራዊት ጥሰው በማለፍ በቤተልሔም በር አጠገብ ከሚገኘው ጒድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣው ስላልፈለገ  በእግዚአብሔር ፊት አፈሰሰው፤ 19ከዚያም “ይህን ከማድረግ እግዚአብሔር ይጠብቀኝ፤ ይህ በሕይወታቸው ቈርጠው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም እንደ መጠጣት አይደለምን?” አለ። ይህን ለማምጣት በሕይወታቸው ቈርጠው ስለ ነበር፣ ዳዊት ሊጠጣው አልፈለገም።

ሦስቱ ኀያላን ሰዎች የሠሩት ይህንን ነበር።

20የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበረ። እርሱም ጦሩን አንሥቶ ሦስት መቶ ሰዎች ገደለ፤ ከዚህም የተነሣ እንደ ሦስቱ ሁሉ ዝነኛ ሆነ። 21ከሦስቱ አንዱ ሆኖ ባይቈጠርም እንኳ፣ እጥፍ ክብር አገኘ፤ አዛዣቸውም ሆነ።

22ከቀብስኤል የመጣውና ታላቅ ጀብዱ የሠራው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ብርቱ ተዋጊ ነበረ። እርሱም እጅግ የታወቁ ሁለት የሞአብ ሰዎችን ገደለ። እንዲያውም አንድ ጊዜ በረዶ ምድርን በሸፈነበት ቀን ወደ አንድ ጒድጓድ ወርዶ አንበሳ ገደለ። 23ደግሞም ቁመቱ አምስት ክንድ
2.3 ሜትር ያህል ነው።
የሆነ አንድ ግብፃዊ ገደለ፤ ግብፃዊው የሸማኔ መጠቅለያ የመሰለ ጦር በእጁ ቢይዝም፣ በናያስ ግን ቆመጥ ይዞ ገጠመው፤ ከግብፃዊው እጅ ጦሩን ነጥቆ በገዛ ጦሩ ገደለው።
24የዮዳሄ ልጅ በናያስ የፈጸመው ጀብዱ ይህ ነበር፤ እርሱም እንደ ሦስቱ ኀያላን ዝነኛ ሆነ። 25ከሠላሳዎቹም ይልቅ የበለጠ ክብር ተጐናጸፈ፤ ይሁን እንጂ ክሦስቱ አንዱ አልነበረም፤ ዳዊትም የክብር ዘቡ አዣዥ አደረገው።
26 ኀያላኑም እነዚህ ነበሩ፤
የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፣
የቤተ ልሔሙ የዱዲ ልጅ ኤልያናን፣

27 ሃሮራዊው ሳሞት፣
ፊሎናዊው ሴሌድ፣

28 የቴቊሔ ሰው የሆነው የዒስካ ልጅ፣
ዒራስ፣ የዓናቶቱ ሰው አቢዔዜር፣

29 ኩሳታዊው ሴቤካይ፣
አሆሃዊው ዔላይ፣

30 ነጦፋዊው ማህራይ፣
የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌድ፣

31 ከብንያም ወገን የጊብዓ ሰው የሆነው የሪባይ ልጅ ኤታይ፣
ጲርዓቶናዊው በናያስ፣

32 የገዓስ ሸለቆዎች ሰው የሆነው ኡሪ፣
ዓረባዊው አቢኤል፣

33 ባሕሩማዊው ዓዝሞት፣
ሰዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፣

34 የጊዞናዊው የአሳን ልጆች፣
የሃራራዊው የሻጌ ልጅ ዮናታን፣

35 የሃራራዊው የሳኮር ልጅ አሒአም፣
የኡር ልጅ ኤሊፋል፣

36 ምኬራታዊው ኦፌር፣
ፍሎናዊው አኪያ፣

37 ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፣
የኤዝባይ ልጅ ነዕራይ፤

38 የናታን ወንድም ኢዮኤል፣
የሃግሪ ልጅ ሚብሐር፣

39 አሞናዊው ጼሌቅ፣
የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ነሃራይ፣

40 ይትራዊው ዒራስ፣
ይትራዊው ጋሬብ፣

41 ኬጢያዊው ኦርዮ፣
የአሕላይ ልጅ ዛባድ፣

42 የሮቤላዊው የሺዛ ልጅ ዓዲና፤
እርሱም የሮቤላውያንና አብረውት
ለነበሩት የሠላሳ ሰዎች አለቃ ነበረ።

43 የማዕካ ልጅ ሐናን፣
ሚትናዊው ኢዮሣፍጥ፣

44 አስታሮታዊው ዖዝያ፣ የአሮዔራዊው
የኮታም ልጆች ሻማና ይዒኤል፣

45 የሺምሪ ልጅ ይዲኤል፣
ወንድሙም ቴዳዊው ዮሐ፣

46 መሐዋዊው ኤሊኤል፣
የኤልነዓም ልጆች ይሪባይና ዮሻውያ፣
ሞዓባዊው ይትማ፣
47ኤሊኤል፣ ዖቤድና ምጾባዊው የዕሢኤል።
Copyright information for AmhNASV