2 Chronicles 26

የይሁዳ ንጉሥ ዖዝያን

26፥1-4 ተጓ ምብ – 2ነገ 14፥21-22፤ 15፥1-3 26፥21-23 ተጓ ምብ – 2ነገ 15፥5-7

1ከዚህ በኋላ የይሁዳ ሕዝብ በሙሉ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት የነበረውን ዖዝያንን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፈንታ አነገሡት። 2አሜስያስ እንደ አባቶቹ ሁሉ ካንቀላፋ በኋላ፣ ኤላትን እንደ ገና የሠራት፣ ወደ ይሁዳም የመለሳት ዖዝያን ነበር።

3ዖዝያን በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀምጦ
ብዙ የዕብራይስጥ ትርጒሞች፣ የሰብዓ ሊቃናትና የሱርስቱ ቅጅ ከዚህ ጋር ይስማማሉ፤ አንዳንድ የዕብራስጥ ቅጆች ግን እንደ እግዚአብሔር ራእይ ባስተማረው ይላሉ።
አምሳ ሁለት ዓመት ገዛ። እናቱ ይኮልያ የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች።
4እርሱም አባቱ አሜስያስ እንደ አደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። 5እግዚአብሔርን መፍራት ባስተማረው በዘካርያስ ዘመን እግዚአብሔርን ፈለገ፤ እግዚአብሔርን በፈለገ መጠንም አምላክ ነገሮችን አከናወነለት።

6በፍልስጥኤማውያን ላይ ዘምቶ የጌትን፣ የየብናንና የአዛጦንን ቅጥሮች አፈረሰ። ከዚያም በአዛጦን አጠገብና በቀሩትም የፍልስጥኤም ግዛቶች ውስጥ ከተሞችን እንደ ገና ሠራ። 7እግዚአብሔርም በፍልስጥኤማውያን፣ በጉርበኣል በሚኖሩ ዐረቦችና በምዑናውያን ላይ ድልን አቀዳጀው። 8አሞናውያን ለዖዝያን ግብር ገበሩለት፤ ኀይሉ ስለ ገነነም ዝናው እስከ ግብፅ ዳርቻ ወጣ።

9ዖዝያንም በኢየሩሳሌም በማዕዘኑ በር፣ በሸለቆው በርና በቅጥሩ ማዕዘን ማማዎች ሠርቶ መሸጋቸው። 10እንዲሁም በየኰረብታው ግርጌና በየሜዳው ላይ ብዙ የቀንድ ከብት ስለ ነበረው፣ በምድረ በዳ የግንብ ማማዎች ሠራ፤ ብዙ የውሃ ጒድጓዶችም ቈፈረ። ግብርና ይወድ ስለ ነበረም በኰረብታዎችና ለም በሆኑ መሬቶች ላይ ዕርሻ የሚያርሱና ወይን የሚተክሉ ሰራተኞች ነበሩት።

11ዖዝያን ከንጉሡ ሹማምት አንዱ በሆነው በሐናንያ መሪነት፣ በጸሓፊው በይዒኤልና በአለቃው በመዕሤያ አማካይነት ተሰብስቦ በተቈጠረው መሠረት በየምድቡ ለጦርነት ዝግጁ ሆኖ የሚወጣ፣ በሚገባ የሠለጠነ ሰራዊት ነበረው። 12በተዋጊዎቹ ላይ የተሾሙት የየቤተ ሰቡ መሪዎች ጠቅላላ ቊጥር ሁለት ሺህ ስድስት መቶ ነበር። 13በእነዚህም የሚመራ ሦስት መቶ ሰባት ሺህ አምስት መቶ ሰው ያለው ሰራዊት አለ፤ ይህም ንጉሡ በጠላቶቹ ላይ በሚያደርገው ዘመቻ ለመሰለፍ የሚበቃ ጠንካራ ኃይል ነበር። 14ዖዝያን ለሰራዊቱ ሁሉ ጋሻ፣ ጦር፣ የራስ ቁር፣ ጥሩር፣ የቀስት ማስፈንጠሪያ ደጋንና የሚወነጨፍ ድንጋይ አደለ። 15በኢየሩሳሌምም፣ ንድፎቻቸው በባለ ሙያዎች የተዘጋጁ፣ በመጠበቂያ የግንብ ማማዎችና በየማዕዘኑ መከላከያዎች ላይ ፍላጻ የሚስፈነጠርባቸውንና ትልልቅ ድንጋዮች የሚወረወርባቸውን መሣሪያዎች አሠራ። እስኪበረታም ድረስ በሚያስደንቅ ሁኔታ ስለታገዘ፣ ዝናው በርቀትና በስፋት ተሰማ።

16ዖዝያን ከበረታ በኋላ ግን ዕብሪቱ ለውድቀት ዳረገው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመግባቱ እግዚአብሔርን በደለ፤ 17ካህኑም ዓዛርያስ ቈራጥ ከሆኑ ከሌሎች ሰማንያ የእግዚአብሔር ካህናት ጋር ተከትሎት ገባ። 18እነርሱም ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ “ዖዝያን ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ማጠን ለተለዩትና የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለካህናቱ እንጂ ለአንተ የተገባ አይደለም፤ እግዚአብሔርን በድለሃልና ከመቅደሱ ውጣ፤ ከእግዚአብሔር አምላክ ዘንድም ክብር አይሆንልህምና” አሉት።

19ጥና በእጁ ይዞ ዕጣን ለማጠን ዝግጁ የነበረው ዖዝያን ተቈጣ፤ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ በዕጣን መሠዊያው ፊት ሆኖ ካህናቱ ላይ እየተቈጣ ሳለ፣ በግንባሩ ላይ ለምጽ
የዕብራይስጡ ቃል በዚህም ሆነ በቍጥር 20፡21 እና 23 ላይ ማንኛውንም ዐይነት የቈዳ በሽታ የሚያመለክት ነው።
ወጣበት።
20ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስና ሌሎቹ ካህናት ሁሉ በተመለከቱት ጊዜ፣ በግንባሩ ላይ ለምጽ እንደ ወጣበት አዩ። ስለዚህ አጣድፈው አስወጡት፤ በእርግጥ እርሱም ራሱ ለመውጣት ቸኵሎ ነበር፤ እግዚአብሔር አስጨንቆታልና።

21ንጉሥ ዖዝያን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ለምጻም ነበረ። ለምጻም በመሆኑም ከቤተ መቅደስ ተወግዶ ነበርና በተለየ ቤት ተቀመጠ
ወይም ከኀላፊነቱ በሚርቅበት ቤት ተብሎ መተርጒም ይቻላል።
። ከዚያም ልጁ ኢዮአታም የቤተ መንግሥቱን አስተዳደር በኀላፊነት ተረክቦ የአገሩን ሕዝብ ይመራ ጀመር።

22በዖዝያን ዘመነ መንግሥት ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተከናወነውን ሌላውን ተግባር ሁሉ የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ጽፎታል። 23ዖዝያንም እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ። ሕዝቡም “ለምጽ አለበት” ብለው የነገሥታቱ በሆነው መቃብር አጠገብ ባለው ቦታ ቀበሩት፤ ልጁም ኢዮአታም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።
Copyright information for AmhNASV