2 Chronicles 29

ሕዝቅያስ ቤተ መቅደሱን አነጻ

29፥1-2 ተጓ ምብ – 1ነገ 18፥2-3

1ሕዝቅያስ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ገዛ። እናቱም አቡ የተባለች፤ የዘካርያስ ልጅ ነበረች። 2አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ።

3በዘመነ መንግሥቱ በመጀመሪያው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሮች ከፈተ፤ አደሳቸው። 4ካህናቱንና ሌዋውያኑን አስገብቶ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይ ላይ በመሰብሰብ፣ 5እንዲህ አላቸው፤ “እናንት ሌዋውያን፤ ስሙኝ! ራሳችሁን አሁኑኑ ቀድሱ፤ የአባቶቻችሁን አምላክ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ ቀድሱ። ርኩስ ነገርንም ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ። 6አባቶቻችን ታማኞች አልነበሩም፣ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ተውትም። ከእግዚአብሔር ማደሪያ ፊታቸውን መለሱ፤ ጀርባቸውንም አዞሩበት። 7የሰበሰቡንም በሮች ዘጉ፤ መብራቶቹንም አጠፉ። ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ዕጣን አላጠኑም፤ በመቅደሱም የሚቃጠል መሥዋዕት አላቀረቡም። 8ስለዚህ የእግዚአብሔር ቊጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወርዶአል፤ እናንተ በገዛ ዓይናችሁ እንደምታዩት ለድንጋጤ፣ ለመደነቂያና ለመዘበቻ አሳልፎ ሰጣቸው። 9በዚህ ምክንያት አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን፣ ሚስቶቻችንም ተማረኩ። 10አሁንም አስፈሪ ቊጣው ከእኛ እንዲመለስ፣ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ለመግባት አስቤአለሁ። 11ልጆቼ ሆይ፤ እንግዲህ ቸል አትበሉ፤ በፊቱ እንድትቆሙና እንድታገለግሉት፣ በፊቱም አገልጋዮቹ እንድትሆኑና ዕጣን እንድ ታጥኑለት እግዚአብሔር መርጦአችኋልና።”

12ከዚያም እነዚሁ ሌዋውያን በሥራው ላይ ተሰማሩ፤ ከቀዓት ዘሮች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፤ ከሜራሪ ዘሮች፣
የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፤
ከጌድሶን ዘሮች፣
የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ዔድን፤

13 ከኤሊጻፋን ዘሮች፣
ሺምሪና ይዒኤል፤
ከአሳፍ ዘሮች፣
ዘካርያስና መታንያ፤

14 ከኤማን ዘሮች፣
ይሒኤልና ሰሜኢ፣
ከኤዶታም ዘሮች፣
ሸማያና ዑዝኤል።

15ወንድሞቻቸውን ከሰበሰቡና ራሳቸውን ከቀደሱ በኋላ፣ ንጉሡ የእግዚአብሔርን ቃል ተከትሎ ባዘዘው መሠረት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማንጻት ገቡ። 16ካህናቱ የእግዚአብሔርን መቅደስ ለማንጻት ወደ ውስጡ ገቡ። በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ያገኙትንም ማናቸውንም የረከሰ ነገር ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ አወጡት። ሌዋውያኑም ተሸክመው በመውሰድ በቄድሮን ሸለቆ ውስጥ ጣሉት። 17ማንጻቱንም በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን ጀምረው በዚያኑ ወር በስምንተኛው ቀን እስከ መቅደስ ሰበሰብ ደረሱ፤ በሚቀጥሉትም ስምንት ቀናት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቀደሱ፤ የመቀደሱም ሥራ በመጀመሪያው ወር በዐሥራ ስድስተኛው ቀን ተጠናቀቀ።

18ከዚያም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው እንዲህ አሉ፤ “የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሙሉ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ ከነዕቃዎቹ ሁሉ፣ ኀብስተ ገጹ የሚቀመጥበትን ጠረጴዛ፣ ከነዕቃዎቹ አንጽተናል። 19ንጉሥ አካዝ ነግሦ ሳለ ታማኝነቱን ትቶ፣ ከቦታቸው ያነሣቸውን ዕቃዎች ሁሉ አዘጋጅተን ቀድሰናቸዋል፤ እነሆ፤ ዕቃዎቹ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠዊያ ፊት ለፊት ናቸው።”

20በማግስቱም ጧት በማለዳ፣ ንጉሥ ሕዝቅያስ የከተማዪቱን ሹማምት በአንድነት ሰብስቦ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ወጣ፤ 21እነርሱም ስለ መንግሥቱ፣ ስለ መቅደሱና ስለ ይሁዳ ሰባት ወይፈኖች፣ ሰባት አውራ በጎች፣ ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶችና ሰባት ተባዕት የፍየል ጠቦቶች ለኀጢአት መሥዋዕት አቀረቧቸው፤ ንጉሡም እነዚህን በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ እንዲያቀርቡ የአሮንን ዘሮች ካህናቱን አዘዘ። 22ካህናቱም ወይፈኖቹን ዐርደው ደሙን በመውሰድ በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ እንደዚሁም ጠቦቶቹን ዐርደው ደሙን በመሠዊያው ላይ ረጩት። 23ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆኑትን ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፤ እነርሱም እጆቻቸውን ጫኑባቸው። 24ንጉሡ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ስለ እስራኤል ሁሉ እንዲቀርብ አዞ ስለ ነበር፣ ካህናቱ ፍየሎቹን ዐርደው ስለ እስራኤል ሁሉ ማስተስረያ እንዲሆን የኀጢአት መሥዋዕት በማድረግ ደሙን በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።

25ንጉሥ ሕዝቅያስም በዳዊት፣ በንጉሡ ባለ ራእይ በጋድና በነቢዩ በናታን በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሌዋውያኑን ጸናጽል፣ በገናና መሰንቆ አስይዞ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መደባቸው፤ ይህም በነቢያት አማካይነት ከእግዚአብሔር የተሰጠ ትእዛዝ ነበር። 26ስለዚህ ሌዋውያኑ የዳዊትን የዜማ ዕቃዎች፣ ካህናቱም መለከቶቻቸውን ይዘው ዝግጁ በመሆን ቆሙ።

27ከዚህ በኋላ ሕዝቅያስ የሚቃጠለው መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ እንዲቀርብ አዘዘ። መሥዋዕቱ ማረግ በጀመረ ጊዜም፣ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት የዜማ ዕቃዎችና በመለከት የታጀበ ዝማሬም ጀመረ። 28መዘምራኑ በሚዘም ሩበትና መለከተኞቹም በሚነፉበት ጊዜም መላው ጉባኤ አጎንብሰው ሰገዱ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪጠናቀቅ ድረስም ይህ ሁሉ ቀጠለ።

29መሥዋዕቱ ሁሉ ቀርቦ ካበቃ በኋላ፣ ንጉሡና አብረውት የነበሩት ሁሉ ተንበርክከው ሰገዱ። 30ንጉሥ ሕዝቅያስና ሹማምቱ፣ ሌዋውያኑ በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ አዘዙ። እነርሱም ውዳሴውን በደስታ ዘመሩ፤ ራሳቸውንም አጎንብሰው ሰገዱ።

31ከዚያም ሕዝቅያስ፣ “እነሆ፤ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችኋል፤ አሁንም ቅረቡ፤ መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ጉባኤው መሥዋዕትና የምስጋና ስጦታ አመጡ፤ ልባቸው የፈቀደ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ።

32ጉባኤውም ያመጣው የሚቃጠለው መሥዋዕት ብዛት ሰባ ወይፈኖች፣ መቶ አውራ በጎችና ሁለት መቶ ተባዕት የበግ ጠቦቶች ናቸው፤ ሁሉም የሚቃጠል መሥዋዕት ሆነው ለእግዚአብሔር የሚቀርቡ ነበሩ። 33ለመሥዋዕት የተቀደሱት እንስሳት ባጠቃላይ ስድስት መቶ ወይፈን፣ ሦስት ሺህ በጎችና ፍየሎች ነበሩ። 34ይሁን እንጂ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ቈዳ ሁሉ ለመግፈፍ ቊጥራቸው እጅግ ጥቂት ነበር፤ ስለዚህ ወገኖቻቸው የሆኑት ሌዋውያን ሥራው እስኪያልቅና ሌሎች ካህናት እስኪቀደሱ ድረስ ረዷቸው፤ ሌዋውያኑም ራሳቸውን ለመቀደስ ከካህናቱ ይልቅ ጠንቃቆች ነበሩና። 35ከሚቃጠለው መሥዋዕት ጋር የሚቀርበውን የኅብረት መሥዋዕት
በትውፊት የሰላም መሥዋዕት ይባላል።
ስብና የመጠጡን ቍርባን ጨምሮ የሚቃጠለው መሥዋዕት እጅግ ብዙ ነበር። በዚህ ሁኔታም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት እንደ ገና ተደራጀ።
36ሕዝቅያስና ሕዝቡ ነገሩ ሁሉ እንዲህ በተፋጠነ ሁኔታ እንዲከናወን እግዚአብሔር ስለረዳቸው ሐሴት አደረጉ።
Copyright information for AmhNASV