2 Kings 22

የሕጉ መጽሐፍ ተገኘ

22፥1-20 ተጓ ምብ – 2ዜና 34፥1-2፡8-28

1ኢዮስያስ ሲነግሥ ዕድሜው ገና ስምንት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሠላሳ አንድ ዓመት ገዛ። እናቱም የባሱሮት አገር ሰው የአዳያ ልጅ ይዲዳ ነበረች። 2ኢዮስያስም  በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነገር አደረገ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም፤ አባቱ ዳዊት በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ።

3በዘመነ መንግሥቱ በዐሥራ ስምንተኛውም ዓመት ኢዮስያስ የሜሶላምን የልጅ ልጅ የኤዜልያስን ልጅ ጸሓፊውን ሳፋንን ወደ  እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ላከው፤ እንዲህም አለው፤ 4“ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ኬልቅያስ ውጣ፤ የበር ጠባቂዎች ከሕዝቡ ሰብስበው ወደ  እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባው ገንዘብ ምን ያህል እንደሆነ ራሱ እንዲቈጥረው አድርግ፤ 5ይህም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንዲቈጣጠሩ ለተሾሙት ሰዎች ይሰጥ፤ እነርሱም  የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለሚያድሱት ይክፈሏቸው፤ 6የሚከፍሉትም ለአናጺዎች፣ ለግንበኞችና ለድንጋይ ጠራቢዎች ነው። እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ እድሳት ሥራ የሚሆኑ ሳንቃዎችና የተጠረቡ ድንጋዮች ይግዙበት። 7ሰዎቹ ታማኞች ስለ ሆኑም የተሰጣቸውን ገንዘብ መቈጣጠር አያስፈልግም።”

8ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ እኮ  በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” ብሎ ሰጠው፤ እርሱም ተቀብሎ አነበበው። 9ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ሄዶ ለንጉሡ፣ “ሹማምትህ  በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ አውጥተዋል፤ ቤተ መቅደሱን እየተቈጣጠሩ ለሚያሠሩትም አስረክበዋል” አለው። 10ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ለንጉሡ፣ “ሊቀ ካህናቱ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” ብሎ ነገረው። ሳፋንም ለንጉሡ ከመጽሐፉ አነበበለት።

11ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ። 12ከዚያም ካህኑን ኬልቅያስን፣ የሳፋን ልጅ አኪቃምን፣ የሚክያስን ልጅ ዓክቦርን፣ ጸሓፊውን ሳፋንንና የንጉሡን የቅርብ አገልጋይ ዓሳያን እንዲህ ሲል አዘዛቸው፤ 13“ሂዱና ስለ እኔ፣ ስለ ሕዝቡና ስለ ይሁዳም ሁሉ በተገኘው በዚህ መጽሐፍ የተጻፈው ምን እንደሆነ  እግዚአብሔርን ጠይቁ፤ ምክንያቱም አባቶቻችን ለዚህ መጽሐፍ ቃል ባለመታዘዛቸው፣ እኛን በተመለከተም በዚሁ ላይ የተጻፈውን ሁሉ ባለመፈጸማቸው፣ በእኛ ላይ የሚነደው  የእግዚአብሔር ቊጣ ታላቅ ነውና።”

14ካህኑ ኬልቅያስ፣ አኪቃም፣ ዓክቦርና፣ ሳፋን፣ ዓሳያም የሐርሐስ የልጅ ልጅ፣ የቲቁዋ ልጅ የአልባሳት ጠባቂውን የሴሌምን ሚስት ነቢዪቱን ሕልዳናን ለመጠየቅ ሄዱ። እርሷም የምትኖረው ኢየሩሳሌም ውስጥ በሁለተኛው ሰፈር ነበር።

15ነቢዪቱም፣ “የእስራኤል አምላክ  እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፤ 16 እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ የይሁዳ ንጉሥ ባነበበው መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ በዚህ ቦታና በሕዝቡ ላይ አመጣለሁ። 17እኔን ስለተውኝና ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣ እጆቻቸው በሠሯቸውም አማልክት ሁሉ
ወይም፣ በሠሩት ሥራ ሁሉ
ስላስቈጡኝ፣ ቊጣዬ በዚህ ቦታ ላይ ይነዳል፣ አይጠፋምም።’ ”
18 እግዚአብሔርን እንድትጠይቁ ወደዚህ ቦታ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ ይህን ንገሩት፣ ‘ስለ ሰማኸው ነገር የእስራኤል አምላክ  እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ 19“ለርግማንና ለጥፋት የተዳረጉ ስለ መሆናቸው በዚህ ቦታና በሕዝቡ ላይ የተናገርኩትን ስትሰማ ልብህ ስለ ተነካና ራስህን  በእግዚአብሔር ፊት ስላዋረድህ፣ ልብስህንም ቀደህ በፊቴ ስላለቀስህ  እግዚአብሔር ሰምቼሃለሁ ብሏል። 20ስለዚህ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ ወደ መቃብር በሰላም ትወርዳለህ፤ በዚህ ቦታም የማመጣውን መከራ ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም።’ ” ሰዎቹም መልሱን ለንጉሡ ይዘውለት ሄዱ።
Copyright information for AmhNASV