Deuteronomy 16

ፋሲካ

16፥1-8 ተጓ ምብ – ዘፀ 12፥14-20፤ ዘሌ 23፥4-8፤ ዘኁ 28፥16-25

1አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በአቢብ ወር ከግብፅ በሌሊት ስላወጣህ፣ የአቢብን ወር ጠብቅ፤ የአምላክህን  የእግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) ፋሲካ አክብርበት። 2 እግዚአብሔር (ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ በሚመርጠው ስፍራ ከበግና ከፍየል ወይም ከመንጋህ አንዱን እንስሳ ለአምላክህ  ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፋሲካ አድርገህ ሠዋው። 3ከቦካ ቂጣ ጋር አትብላው፤ ከግብፅ የወጣኸው በችኮላ ነውና ከግብፅ የወጣህበትን ጊዜ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ታስብ ዘንድ የመከራ ቂጣ ሰባት ቀን ብላ። 4በምድርህ ሁሉ ላይ በአንተ ዘንድ ለሰባት ቀን እርሾ አይገኝ፤ በመጀመሪያው ዕለት ምሽት ከምትሠዋውም ላይ ማናቸውንም ሥጋ ጧት ድረስ እንዲቈይ አታድርግ። 5አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ በማናቸውም ከተማ ፋሲካን መሠዋት አይገባህም፤ 6ነገር ግን ለስሙ ማደሪያ ይሆን ዘንድ አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ፣ ፀሓይ ስትጠልቅ ምሽቱ
ወይም፣ ፀሓይ ስትወጣ ንጋቱ ላይ
ላይ ከግብፅ በወጣህበት ሰዓት ዓመታዊ መታሰቢያ በዚያ ፋሲካን ሠዋ።
7ሥጋውንም ጠብሰህ አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚመርጠው ስፍራ ብላ፤ ሲነጋም ወደ ድንኳንህ ተመልሰህ ሂድ።

8ስድስት ቀን ያልቦካ ቂጣ ብላ፤ በሰባተኛው ቀን ለአምላክህ  ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የተቀደሰ ጉባኤ አድርግ፤ ሥራም አትሥራበት።

የመከር በዓል

16፥9-12 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥15-22፤ ዘኁ 28፥26-31

9እህልህን ማጨድ ከምትጀምርበት ዕለት አንሥቶ ሰባት ሳምንት ቊጠር፤ 10ከዚያም በኋላ አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በባረከህ መጠን፣ በፈቃድህ የምታመጣውን ስጦታ በማቅረብ በመከሩ በዓል አምላክህን  እግዚአብሔርን (ኤሎሂም ያህዌ) አክብር። 11አንተ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ፣ ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችህ፣ በከተሞችህ ያለ ሌዋዊና መጻተኛ በመካከልህ የሚኖሩ አባት የሌላቸውና መበለቶች አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ለስሙ ማደሪያ እንዲሆን በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ  በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ደስ ይበላችሁ። 12አንተም በግብፅ ባሪያ እንደ ነበርህ አስታውስ፤ ይህንንም በጥንቃቄ ጠብቅ።

የዳስ በዓል

16፥13-17 ተጓ ምብ – ዘሌ 23፥33-43፤ ዘኁ 29፥12-39

13የእህልህን ምርት ከዐውድማህ፣ ወይንህንም ከመጭመቂያህ ከሰበሰብህ በኋላ፣ የዳስን በዓል ሰባት ቀን አክብር። 14በበዓልህ አንተ፣ ወንድና ሴት ልጅህ፣ ወንድና ሴት አገልጋይህ፣ በከተማው ያለ ሌዋዊ፣ መጻተኛ፣ አባት አልባውና መበለቲቱ ደስ ይበላችሁ። 15 እግዚአብሔር (ያህዌ) በመረጠው ስፍራ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በዓሉን ሰባት ቀን አክብር፤ አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በእህል ምርትህና በእጅህ ሥራ ሁሉ ይባርክሃል፤ ደስታህም ፍጹም ይሆናል።

16ወንዶችህ ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ፣ በቂጣ በዓል፣ በመከር በዓልና በዳስ በዓል ላይ፣ እርሱ በሚመርጠው ስፍራ በአምላክህ  በእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) ፊት ይቅረቡ፤ ማንም ሰው  በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ባዶ እጁን አይቅረብ። 17አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በባረከህ መጠን እያንዳንዱ እንደ ችሎታው ይስጥ።

ስለ ፍርድ አሰጣጥ

18አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በሚሰጥህ ከተሞች ሁሉ ለየነገዶችህ ዳኞችንና አለቆችን ሹም፤ እነርሱም ሕዝቡን በቅን ፍርድ ይዳኙ። 19ፍርድ አታዛባ፤ አድልዎ አታድርግ፤ ጒቦም አትቀበል፤ ጒቦ የጠቢባንን ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና። 20በሕይወት እንድትኖርና አምላክህ  እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚሰጥህን ምድር እንድትወርስ፣ ቅን ፍርድን ብቻ ተከተል።

ሌሎችን አማልክት ስለ ማምለክ

21ለአምላክህ  ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) በምትሠራው መሠዊያ አጠገብ የአሼራን ምስል የዕንጨት ዐምድ አታቁም
ወይም፣ ለአሼራ ብለህ ምንም ዐይነት ዛፍ አትትከል
22አምላክህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) የሚጠላውን ማምለኪያ ዐምድ ለአንተ አታቁም።
Copyright information for AmhNASV