Exodus 21

1“በፊታቸው የምትደነግጋቸው ሥርዐቶች እነዚህ ናቸው፤

ዕብራዊ አገልጋይ

21፥2-6 ተጓ ምብ – ዘዳ 15፥12-18 21፥2-11 ተጓ ምብ – ዘሌ 25፥39-55

2“ዕብራዊ አገልጋይ ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፤ በሰባተኛው ዓመት ግን ያለ ምንም ክፍያ በነጻ ይሂድ። 3ብቻውን መጥቶ ከሆነ፣ ብቻውን በነጻ ይሂድ፤ ነገር ግን ሲመጣ ባለ ሚስት ከሆነ፣ እርሷ አብራው ትሂድ። 4ጌታው ሚስት አጋብቶት ወንድ ወይም ሴት ልጅ ከወለደችለት፣ ሴትዮዋና ልጆቿ የጌታቸው ይሆናሉ፤ ሰውዬው ብቻ በነጻ ይሂድ።

5“ነገር ግን አገልጋዩ፤ ‘ጌታዬን፤ ሚስቴንና ልጆቼን እወዳለሁ ነጻ ሆኜ አልሄድም’ ቢል፣ 6ጌታው ወደ ዳኞች
ወይም፣ ወደ ፈራጆች
ይውሰደው፤ ወደ በር ወይም ወደ በሩ መቃን ወስዶ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ከዚያም ዕድሜ ዘመኑን የእርሱ አገልጋይ ይሆናል።

7“አንድ ሰው ሴት ልጁን አገልጋይ እንድትሆን ቢሸጣት፣ እንደ ወንዶቹ አገልጋዮች በነጻ መሸኘት የለባትም። 8ለእርሱ ትሆነው ዘንድ የመረጣትን ጌታዋን ደስ ባታሰኝ፣
ወይም፣ ጌታዋ ይሆን ዘንድ አይምረጣት
በዎጆ ይስደዳት፤ ለባዕዳን ይሸጣት ዘንድ መብት የለውም፤ ምክንያቱም ለእርሷ ያለውን ታማኝነት አጓድሏልና።
9ለወንድ ልጁ ትሆን ዘንድ መርጧት ከሆነ እንደ ራሱ ልጅ የሚገባትን መብት ይስጣት። 10ሌላ ሴት ቢያገባ፣ ለመጀመሪያ ሚስቱ ምግቧን፣ ልብሷንና የጋብቻ መብቷን አይከልክላት። 11እነዚህን ሦስት ነገሮች የማያሟላላት ቢሆን፣ ያላንዳች የገንዘብ ክፍያ በነጻ መሄድ ይኖርባታል።

በሕይወት ላይ ለሚደርስ ጉዳት

12“ሰውን ደብድቦ የገደለ ሞት ይገባዋል። 13ሆኖም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፈቅዶ ሰውየው ሳያውቅ በድንገት አድርጎት ከሆነ፣ እኔ ወደምወስነው ስፍራ ይሽሽ። 14አንድ ሰው በተንኰል ሆን ብሎ ሌላውን ቢገድል፣ ከመሠዊያዬ ተወስዶ ይገደል።

15“አባቱን ወይንም እናቱን የሚመታ
ወይም፣ የሚገድል
ይገደል።

16“አንዱ ሌላውን ጠልፎ የሸጠ ወይም በተያዘ ጊዜ ከእጁ ላይ የተገኘበት ይገደል።

17“አባቱን ወይንም እናቱን የሚሰድብ ይገደል።

18ሰዎች ተጣልተው አንዱ ሌላውን በድንጋይ ወይም በቡጢ
ወይም፣ በዕቃ
ቢመታውና ተመቺው ሳይሞት በአልጋ ላይ ቢውል፣
19በትሩንም ይዞ ደጅ ለደጅ የሚል ቢሆን፣ በዱላ የመታው ሰው አይጠየቅበትም፤ ሆኖም ለተጐጂው ሰው ለባከነበት ጊዜ ገንዘብ ይክፈል፤ ፈጽሞ እስኪድን ክትትል ያድርግለት።

20“አንድ ሰው ወንድ ወይም ሴት ባሪያውን በዱላ ቢመታና ባሪያውም በዚህ የተነሣ ቢሞት መቀጣት አለበት፤ 21ነገር ግን ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ባሪያው ቢነሣ መቀጣት የለበትም፤ ባሪያው ንብረቱ ነውና።

22“በጥል ላይ ያሉ ሰዎች ነፍሰ ጡር ሴት ቢመቱና እርሷም ያለጊዜዋ ብትወልድ፣
ወይም፣ ቢያስወርዳት
ጉዳቱም ለክፉ የማይሰጥ ቢሆን፣ ጉዳት ያደረ ሰባት ሰው የሴትዮዋ ባል የጠየቀውንና ፈራጆቹ የፈቀዱትን ካሣ ሁሉ መክፈል አለበት።
23ነገር ግን የከፋ ጉዳት ቢደርስ ሕይወት በሕይወት፣ 24ዓይን በዓይን፣ ጥርስ በጥርስ፣ እጅ በእጅ፣ እግር በግር፣ 25ቃጠሎ በቃጠሎ፣ ቍስል በቍስል፣ ግርፋት በግርፋት ታስከፍላለህ።

26“አንድ ሰው የወንድ ወይም የሴት አገልጋዩን ዐይን መትቶ ቢያጠፋ፣ ስለ ዐይን ካሣ አገልጋዩን ነጻ ይልቀቀው። 27የወንድ ወይም የሴት አገልጋዩን ጥርስ ቢሰብር፣ ስለ ጥርስ ካሣ አገልጋዩን ነጻ ይልቀቀው።

28“በሬ አንድን ወንድ ወይም ሴት ወግቶ ቢገድል፣ በሬው በድንጋይ ተወግሮ ይሙት፤ ሥጋውም አይበላ፤ ነገር ግን የበሬው ባለቤት በኀላፊነት አይጠየቅም። 29ሆኖም በሬው የመውጋት ዐመል ያለበት ሆኖ ለባለቤቱም ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ሳለ በበረት ሳያስቀረው ቀርቶ አንድን ወንድ ወይም ሴት ቢገድል፣ በሬው በድንጋይ ይወገር፤ ባለቤቱም እንዲሁ ተወግሮ ይሙት። 30ሆኖም ካሣ እንዲከፍል ከተጠየቀ፣ የተጠየቀውን ሁሉ በመክፈል ሕይወቱን ይዋጅ። 31አንድ በሬ አንድን ወንድ ወይም ሴት ልጅ ቢወጋ በዚሁ ሕግ መሠረት ይፈጸም። 32አንድ በሬ ወንድ ወይም ሴት ባሪያን ቢወጋ ባለቤቱ ሠላሳ የብር ሰቅል
ወደ 0.3 ኪሎ ግራም ይደርሳል
ለባሪያው ጌታ መክፈል አለበት፤ በሬውም በድንጋይ ይወገር።
33“አንድ ሰው ጒድጓድን ከፍቶ ቢተው፣ ወይም ጒድጓድ ቆፍሮ ሳይከድነው ቢቀርና በሬ ወይም አህያ ቢገባበት፣ 34የጒድጓዱ ባለቤት ኪሳራ ይክፈል፤ ለባለቤቱ መክፈል አለበት፤ የሞተውም እንስሳ ለእርሱ ይሆናል።

35“የአንድ ሰው በሬ የሌላውን ሰው በሬ ወግቶ ቢገድለው፣ በሕይወት ያለውን በሬ ሽጠው ገንዘቡንና የሞተውን እንስሳ እኩል ይካፈሉ። 36ሆኖም በሬው የመዋጋት ዐመል ያለው መሆኑ ከታወቀ፣ ባለቤቱም በረት ሳይዘጋበት ቢቀር፣ ባለቤቱ በሬውን በበሬው ፈንታ ይክፈል፤ የሞተውም እንስሳ ለእርሱ ይሆናል።
Copyright information for AmhNASV