Exodus 22

ንብረትን ስለ መጠበቅ

1“አንድ ሰው በሬ ወይም በግ ሰርቆ ቢያርድ ወይም ቢሸጥ በአንድ በሬ ምትክ አምስት በሬዎች፤ በአንድ በግ ምትክ አራት በጎች ይክፈል።

2“አንድ ሌባ በር ሲሰብር ተይዞ ቢደበደብና ቢሞት፣ ተከላካዩ የደም ባለ ዕዳ አይሆንም፤ 3ነገር ግን ፀሓይ ከወጣች በኋላ ከተፈጸመ፣
ወይም፣ ከመታው
ሰውየው በነፍስ ግድያ ይጠየቃል።

“ሌባ የሰረቀውን መክፈል አለበት፤ ምንም ከሌለው ግን የሰረቀውን ይከፍል ዘንድ ይሸጥ።

4“የሰረቀው እንስሳ በሬ ወይም አህያ ወይም በግ ከነሕይወቱ በእጁ ከተያዘ ዕጥፍ መክፈል አለበት።

5“አንድ ሰው ከብቶቹን በመስክ ወይም በወይን ቦታ አሰማርቶ እንዲሁ ስድ ቢለቅቃቸውና የሌላውን ሰው መስክ ቢግጡ፣ ምርጥ ከሆነው ከራሱ መስክ ወይም የወይን ቦታ መክፈል አለበት።

6“እሳት ተነሥቶ ወደ ቍጥቋጦ ቢዘምትና ክምርን ወይም ያልታጨደን እህል ወይም አዝመራውን እንዳለ ቢበላ፣ እሳቱን ያቀጣጠለው ሰው ካሳ ይክፈል።

7“አንድ ሰው ብሩ ወይም ንብረቱ ያለ ሥጋት ይጠበቅለት ዘንድ ለጎረቤቱ ሰጥቶ ሳለ ቢሰርቅበትና፣ ሌባው ቢያዝ ዕጥፍ ይክፈል፤ 8ሌባው ካልተያዘ ግን፣ የቤቱ ባለቤት በንብረቱ ስርቆት ላይ እጁ ይኑርበት ወይም አይኑርበት ይታወቅ ዘንድ ዳኞች ፊት
በዚህም ሆነ በቍጥር 9 ላይ ያለው፣ እግዚአብሔር ፊት
ይቅረብ።
9አንድ ሰው በሬን፣ አህያን፣ በግን፣ ልብስን ወይም ማናቸውንም ንብረት ያለ አግባብ በባለቤትነት ይዞ ሳለ፣ ‘የእኔ ነው’ ባይ ቢመጣና ክርክር ቢነሣ፣ ባለ ጕዳዮቹ ነገሩን ለዳኞች ያቅርቡት፤ ዳኞቹ ጥፋተኛ ነው ያሉትም
ወይም፣ እግዚአብሔር ጥፋተኛ ነው ያለውም
ለጎረቤቱ ዕጥፉን ይክፈል።

10“አንድ ሰው አህያ፣ በሬ፣ በግ ወይም ማናቸውንም እንስሳ በጎረቤቱ ዘንድ በዐደራ አስቀምጦ ሳለ እንስሳው ቢሞት ወይም ጕዳት ቢደርስበት ወይም ሰው ሳያይ ተነድቶ ቢወሰድ፣ 11በሁለቱ መካከል ያለው አለመግባባት መፍትሔ የሚያገኘው፣ ጎረቤቱ የሌላውን ሰው ንብረት እንዳልወሰደ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት በመማል ነው። ባለቤቱም ይህን መቀበል አለበት፤ የካሳም ክፍያ አይጠየቅም። 12እንስሳው ከጎረቤት ተሰርቆ ከሆነ ግን፣ ለባለቤቱ ካሳ መክፈል አለበት። 13በዱር አራዊት ተበልቶ ከሆነ፣ ከአውሬ የተረፈውን ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ፣ ስለ ተበላው እንስሳ ካሳ እንዲከፍል አይጠየቅም።

14“አንድ ሰው ከጎረቤቱ እንስሳ ተውሶ ሳለ፣ ባለቤቱ በሌለበት ቢጐዳ ወይም ቢሞት ካሳ መክፈል አለበት። 15ባለቤቱ ከእንስሳው ጋር ከሆነ ግን፣ ተበዳሪው መክፈል የለበትም፤ እንስሳው ከተከራየም ለኪራይ የተከፈለው ገንዘብ ኪሳራውን ይሸፍናል።

ማኅበራዊ ኀላፊነት

16“አንድ ሰው ያልታጨችን ልጃገረድ አታልሎ ክብረ ንጽሕናዋን ቢያጐድል፣ የማጫዋን ዋጋ ከፍሎ ሚስት ያድርጋት። 17እርሷን ለእርሱ የልጅቷ አባት በሚስትነት ለመስጠት ከቶ የማይፈቅድ ቢሆን፣ ለድንግሎች መከፈል የሚገባውን ማጫ አሁንም ቢሆን መክፈል ይገባዋል።

18“መተተኛ ሴት በሕይወት እንድትኖር አትፍቀድ።

19“ከእንስሳ ጋር ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽም ሰው ይገደል።

20ለእግዚአብሔር (ያህዌ) በቀር ለሌላ አማልክት የሚሠዋ ይጥፋ
የዕብራይስጡ ቃል አንድን ነገር ወይም አንድን ሰው ፈጽሞ በማጥፋት ሙሉ ለሙሉ ለእግዚአብሔር መስጠትን የሚያመለክት ነው።


21“መጻተኛውን አትበድሉት ወይም አታስጨንቁት፤ እናንተ በግብፅ መጻተኛ ነበራችሁና።

22“ባል በሞተባት ወይም አባትና እናት በሌለው ልጅ ላይ ግፍ አትዋሉ። 23ግፍ ብትውሉባቸውና ወደ እኔ ቢጮኹ፣ ጩኸታቸውን በርግጥ እሰማለሁ። 24ቍጣዬ ይነሣል፤ በሰይፍም እገድላችኋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ መበለቶች፣ ልጆቻችሁም አባት የለሽ ይሆናሉ።

25“ከሕዝቤ መካከል ችግረኛ ለሆነው ለአንዱ ገንዘብ ብታበድሩ፣ እንደ ዐራጣ አበዳሪ አትሁኑ፤ ወለድ አትጠይቁት
ወይም፣ ከልክ በላይ የሆነ ወለድ አትጠይቁ
26የጎረቤትህን ልብስ መያዣ አድርገህ ብትይዝ ሲመሽ መልስለት፤ 27ምክንያቱም ለሰውነቱ መሸፈኛ ያለው ልብስ ያ ብቻ ነው፤ ሌላ ምን ለብሶ ይተኛል? ወደ እኔ ሲጮኽ እኔ እሰማለሁ፤ እኔ ርኅሩኅ ነኝና።

28“በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ላይ የስድብ ቃል አታሰማ
ወይም፣ ዳኞችን አትሳደብ
፤ ወይም የሕዝብህን መሪ አትርገም።

29“የእህልህን ወይም የወይን ጠጅህን በኵራት ለእኔ ከማቅረብ ወደ ኋላ አትበል።

“የወንድ ልጆችህን በኵር ለእኔ ስጠኝ።
30ከቀንድ ከብትህና ከበጎችህም እንዲሁ አድርግ፤ ለሰባት ቀን ከእናቶቻቸው ጋር ይቈዩ፤ በስምንተኛው ቀን ግን ለእኔ ሰጠኝ።

31“እናንተ ለእኔ ቅዱስ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ ስለዚህ አውሬ የዘነጠለውን የእንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ለውሾች ስጡት።

Copyright information for AmhNASV