Exodus 23

የፍትህና የምሕረት ሕጎች

1የሐሰት ወሬ አትንዛ፤ ተንኰል ያለበትን ምስክርነት በመስጠት ክፉውን ሰው አታግዝ።

2“ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል፤ በሕግ ፊት ምስክርነት ስትሰጥ፣ ከብዙዎቹ ጋር ተባብረህ ፍትሕ አታጣምም። 3በዳኝነት ጊዜ ለድኻው አታድላ።

4“የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ሲባዝን ብታገኘው ወደ እርሱ መልሰው። 5የሚጠላህ ሰው አህያ፣ ጭነት ከብዶት ወድቆ ብታየው ርዳው እንጂ ትተኸው አትሂድ።

6“በዳኝነት ጊዜ በድኻው ላይ ፍርድ አታጓድልበት። 7ከሐሰት ክስ ራቅ፤ በደል የሌለበትን ወይም ትክክለኛውን ሰው ለሞት አሳልፈህ አትስጥ፣ በደለኛውን ንጹሕ አላደርግምና።

8“ጒቦ አትቀበል፤ ጒቦ፣ አጥርተው የሚያዩትን ሰዎች ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።

9“መጻተኛውን አትጨቁን፤ በግብፅ መጻተኛ ስለ ነበራችሁ፣ መጻተኛ ምን እንደሚሰማው እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።

የሰንበት ሕጎች

10“ስድስት ዓመት በእርሻህ ላይ ዝራ፤ አዝመራንም ሰብስብ፤ 11ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን ሳትጠቀምባትና ሳታርሳት እንዲሁ ተዋት፤ ከዚያም በወገንህ መካከል ያሉት ድኾች ከእርሷ ምግብ ያገኛሉ፤ የዱር አራዊትም ከእነርሱ የተረፈውን ይበላሉ። በወይን ቦታህና በወይራ ዛፎችህም ላይ እንዲሁ አድርግ።

12“ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ።

13ያልኋችሁን ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ተጠንቀቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይስሙ።

ሦስቱ ዐውደ ዓመታዊ በዓላት

14በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓልን ታከብራላችሁ።

15“ያልቦካ የቂጣ በዓልን አክብር፤ እንዳዘዝኩህ ሰባት ቀን እርሾ የሌለውን ቂጣ ብላ፤ ይህንንም በአቢብ ወር በተወሰነ ቀን አድርግ፤ በዚያ ወር ከግብፅ ወጥተሃልና።

“ማንም በፊቴ ባዶ እጁን አይቅረብ።

16“በማሳህ ላይ በዘራኸው እህል በኵራት የመከርን በዓል አክብር።

“በዓመቱ መጨረሻ በማሳህ ላይ ያለውን እህልህን ስትሰበስብ የመክተቻውን በዓል አክብር።

17“በዓመት ሦስት ጊዜ ወንድ ሁሉ በጌታ  በእግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) ፊት ይቅረብ።

18የመሥዋዕትን ደም እርሾ ካለበት ነገር ጋር አድርገህ ለእኔ አታቅርብ።

“የበዓል መሥዋዕቴ ስብ እስከ ንጋት ድረስ አይቆይ።

19“የምድርን ምርጥ ፍሬ በኵራት ለአምላክህ  ለእግዚአብሔር (ኤሎሂም ያህዌ) አምጣ።

“ጠቦት ፍየልን በእናቱ ወተት አትቀቅል።

የእግዚአብሔር መልአክ መንገድ ስለ መምራቱ

20“እነሆ፤ በጒዞ ላይ ሳለህ የሚጠብቅህንና ወዳዘጋጀሁልህ ስፍራ የሚያስገባህንመልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ። 21በጥንቃቄ ተከተለው፤ የሚናገረውንም ልብ ብለህ አድምጠው፤ አታምፅበት። ስሜ በርሱ ላይ ነውና ዐመፅህን ይቅር አይልም። 22የሚናገረውን በጥንቃቄ ብታደምጥና ያልኩህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህን እቃወማለሁ። 23መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ አንተንም ወደ አሞራውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ያስገባሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ። 24ለአማልክቶቻቸው አትስገድ፤ ወይም አታምልካቸው፤ ወይም ልምዳቸውን አትከተል፤ እነርሱን ማፈራረስ አለብህ፤ የአምልኮ ድንጋዮቻቸውንም ሰባብር። 25አምላክህን  እግዚአብሔርን (ያህዌ) አምልክ፤ በረከቱም በምትበላውና በምትጠጣው ላይ ይሆናል፤ በሽታንም ከአንተ ዘንድ አርቃለሁ። 26በምድርህም የሚያስወርዳት ወይም መካን ሴት አትኖርም፤ ረጅም ዕድሜም እሰጥሃለሁ።

27“በሚያጋጥሙህ አሕዛብ ሁሉ ላይ ማስፈራቴን በፊትህ እልካለሁ፤ ግራም አጋባቸዋለሁ፤ ጠላቶችህ ሁሉ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ። 28ኤዊያውያንን፣ ከነዓናውያንን፣ ኬጢያውያንን ከመንገድህ ለማስወጣት ተርብን በፊትህ እሰዳለሁ። 29ነገር ግን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አላወጣቸውም፤ ምክንያቱም ምድሪቱ፣ ባድማ ሆና፣ የዱር አራዊት ይበዙባችኋል። 30ቍጥርህ ጨምሮ ምድሪቱን ለመውረስ እስክትበቃ ድረስ ጥቂት በጥቂት ከፊታችሁ አባርራቸዋለሁ።

31“ድንበርህን ከቀይ ባሕር
በዕብራይስጥ፣ ያም ሱፍ ይባላል፤ ይኸውም፣ የደንገል ባሕር ማለት ነው።
እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፣
የሜዲትራንያን
ከምድረ በዳው እስከ ወንዙ
የኤፍራጥስ
ድረስ አደርገዋለሁ፤ በምድሪቱም ላይ የሚኖሩትን ሰዎች አሳልፌ እሰጥሃለሁ፤ አንተም አሳደህ ከፊትህ ታስወጣቸዋለህ።

32ከእነርሱም ሆነ ከአማልክቶቻቸው ጋር ኪዳን አታድርግ። 33በምድርህ ላይ እንዲኖሩ አትፍቀድላቸው፤ አለዚያ እኔን እንድትበድል ያደርጉሃል፤ አማልክቶቻቸውን ማምለክ በርግጥ ወጥመድ ይሆንብሃልና።”
Copyright information for AmhNASV