Ezekiel 33

ሕዝቅኤል ጒበኛው

1  የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘በምድር ላይ ሰይፍን ሳመጣ፣ የምድሪቱ ሕዝብ ከሰዎቻቸው አንዱን መርጠው ጒበኛ ቢያደርጉት፣ 3እርሱም በምድሪቷ ላይ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ቢነፋ፣ 4ከዚያም ማንም መለከቱን ሰምቶ ባይጠነቀቅ፣ ሰይፍም መጥቶ ሕይወቱን ቢያጠፋ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል። 5የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ባለመጠንቀቁ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅ ኖሮ ግን ራሱን ባዳነ ነበር። 6ነገር ግን ጒበኛ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ሳይነፋ ቢቀርና ከመካከላቸው የአንዱን ሰው ሕይወት ሰይፍ ቢያጠፋ፣ ያ ሰው ስለ ኀጢአቱ ይወሰዳል፤ ጒበኛውን ግን ስለ ሰውዬው ደም ተጠያቂ አደርገዋለሁ።’

7“የሰው ልጅ ሆይ፤ አንተን ለእስራኤል ቤት ጒበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የምናገረውን ቃል ስማ፤ ማስጠንቀቂያዬንም ስጣቸው። 8ክፉውን፣ ‘አንተ ክፉ ሰው፤ በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ፣ እርሱን ከመንገዱ እንዲመለስ ባታደርገው፣ ያ ክፉ ሰው በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ስለ ደሙ ተጠያቂ ትሆናለህ። 9ነገር ግን ክፉውን ሰው ከመንገዱ እንዲመለስ ነግረኸው እሺ ባይል፣ እርሱ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ራስህን አድነሃል።

10“የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘እንዲህ ትላላችሁ፤ “በደላችንና ኀጢአታችን ከብዶናል፤ ከዚህም
ወይም በእርሱ
የተነሣ ልንጠፋ ነው፤ ታዲያ እንዴት መኖር እንችላለን?’
11እንዲህ በላቸው፤ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ  እግዚአብሔር፤ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም። ተመለሱ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?’

12“አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች እንዲህ በላቸው፤ ‘ጻድቅ ሰው ትእዛዝን በተላለፈ ጊዜ የቀድሞ ጽድቁ አያድነውም፤ ኀጢአተኛ ሰው ከኀጢአቱ ከተመለሰ፣ ከቀድሞ ክፋቱ የተነሣ አይጠፋም። ጻድቅ ሰው ኀጢአት ቢሠራ፣ በቀድሞ ጽድቁ ምክንያት በሕይወት እንዲኖር አይደረግም።’ 13ጻድቁን ሰው በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ብለው፣ እርሱም ጽድቁን ተማምኖ ክፋት ቢሠራ፣ ከጽድቅ ሥራው አንዱም አይታሰብለትም፤ በኀጢአቱም ምክንያት ይሞታል። 14እንዲሁም ክፉውን ሰው፣ ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ብለው፣ እርሱም ከኀጢአቱ ተመልሶ ቀና የሆነውንና ትክክለኛውንም ነገር ቢያደርግ፣ 15ለሰጠው ብድር የተቀበለውን መያዣ ቢመልስ፣ የሰረቀውንም መልሶ ቢሰጥ፣ ሕይወት የሚሰጡትን ትእዛዛት ቢከተል፣ ክፉ ነገርንም ባያደርግ፣ በእርግጥ እርሱ በሕይወት ይኖራል፤ አይሞትምም። 16ከሠራው ኀጢአት አንዱም አይታሰብበትም፤ ቀናውንና ትክክለኛውን አድርጓልና፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።

17“ይህም ሆኖ የአገርህ ሰዎች፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላሉ፤ ቀና ያልሆነው ግን የእነርሱ መንገድ ነው። 18ጻድቅ ሰው የጽድቁን ሥራ ትቶ ክፉ ነገር ቢያደርግ፣ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል። 19ክፉም ሰው ከክፉ ሥራው ተመልሶ ቀናውንና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ፣ ይህን በማድረጉ በሕይወት ይኖራል። 20ይሁን እንጂ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ፤ ነገር ግን በእያንዳንዳችሁ ላይ እንደ መንገዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።”

የኢየሩሳሌም መውደቅ

21በተማረክን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በአምስተኛው ቀን፣ ከኢየሩሳሌም ያመለጠ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ፣ “ከተማዪቱ ወደቀች!” አለኝ። 22ሰውየው ከመድረሱ በፊት በነበረው ምሽት፣  የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ላይ ነበረች፤ በማለዳም ሰውየው ወደ እኔ ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሔር አፌን ከፈተ፤ አፌም ተከፈተ፤ ከዚያ በኋላ ዝም አላልሁም።

23ከዚያም  የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤ 24“የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር በፍርስራሾች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ ‘አብርሃም አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ ያም ሆኖ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ግን ብዙዎች ነን፤ በእርግጥ ምድሪቱ ርስት ሆና ተሰጥታናለች’ ይላሉ። 25ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ ‘ጌታ  እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሥጋውን ከነደሙ ትበላላችሁ፤ ዐይኖቻችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፤ ደምም ታፈሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ታስባላችሁ? 26በሰይፋችሁ ትመካላችሁ፤ አስጸያፊ ነገሮችን ትፈጽማላችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የባልንጀራችሁን ሚስት ታረክሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ይገባችኋል?’

27“እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ  እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ፤ በፍርስራሾች ውስጥ የተረፉት በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በገጠር ያሉትን ቦጫጭቀው እንዲበሏቸው ለዱር አራዊት እሰጣቸዋለሁ፤ በምሽግና በዋሻ ያሉትም በቸነፈር ይሞታሉ። 28ምድሪቱን ጠፍና ባድማ አደርጋታለሁ፤ የምትመካበት ጒልበቷ እንዳልነበረ ይሆናል፤ የእስራኤልም ተራሮች ማንም እንዳያልፍባቸው ባድማ ይሆናሉ። 29ካደረጓቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሣ፤ ምድሪቱን ጠፍና ባድማ በማደርግበት ጊዜ፣ እኔ  እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’

30“አንተን በሚመለከት፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ የአገርህ ሰዎች በየቤቱ በርና ግድግዳ ሥር ሆነው ስለ አንተ ይነጋገራሉ፤ እርስ በራሳቸውም እንዲህ ይባባላሉ፤ ‘ኑና  ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት እንስማ።’ 31ሁል ጊዜ እንደሚያደርጉት ሕዝቤ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ቃልህንም ለመስማት ከፊትህ ይቀመጣሉ፤ ነገር ግን አይፈጽሙትም። በከንፈራቸው ብዙ ፍቅርን ይገልጣሉ፤ ልባቸው ያረፈው ግን ተገቢ ባልሆነ ጥቅም ላይ ነው። 32ቃልህን ሰምተው ሥራ ላይ የማያውሉት በመሆናቸው፣ አንተ ለእነርሱ በአማረ ድምፅ የፍቅር ዘፈን የሚዘፍን፣ በዜማ መሣሪያም አሳምሮ የሚጫወት ሙዚቀኛ ሆነህላቸዋል።

33“ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ደግሞም በርግጥ ይሆናል፣ በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበረ፣ ያውቃሉ።”
Copyright information for AmhNASV